የምገባው  ትሩፋት

You are currently viewing የምገባው  ትሩፋት

ለአንድ ሀገር እድገትና ብልፅግና ቁልፍ ሚና የሚጫወተውን ብቃት ያለው የሰው ሀይል ለማፍራት እውቀት በሚገበይባቸው ትምህርት ቤቶች ላይ የሚሰራው ስራ ወሳኝ ነው፡፡ በትምህርት ቤቶች ለልጆች የተመጣጠነ ምግብ ማቅረብ ጤናማ፣ በትምህርታቸው ውጤታማ፣ አዳዲስ ሀሳቦችን ማፍለቅና በጥልቀት በማሰብ ችግሮችን መፍታት የሚችሉ ዜጎችን ለማፍራት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ጥናቶች ያመለክታሉ፡፡

የዓለም ምግብ ፕሮግራም እ.ኤ.አ በ2017 ዓ.ም Master of Card Foundation ጋር በመሆን በኢትዮጵያ ያጠናው ጥናት እንደሚያሳየው፣ በሀገር በቀል ምገባ አማካይነት በአንድ ልጅ የትምህርት ዘመን ላይ ፈሰስ የምትደረግ እያንዳንዷ ዶላር የልጁን/ቷን ትምህርት፣ ጤና እና ምርታማነት በማሻሻል በአማካይ የ7 ነጥብ 2 የአሜሪካን ዶላር ትርፍ ታስገኛለች፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ በተለይ ዝቅተኛ የኢኮኖሚ አቅም ያላቸው ወላጆች፤ ለልጆቻቸው አስፈላጊውን ምግብ እንዲሁም የትምህርት ቁሳቁስ አሟልቶ መላክ ፈተና ሆኖባቸው ቆይቷል፡፡ በዚህም የተነሳ ቁርሳቸውን በአግባቡ ሳይመገቡ፣ ባዶ የምሳ ሳህን ቋጥረው ወደ ትምህርት ቤት የሚሄዱ ተማሪዎች ቁጥር ቀላል አልነበረም፡፡

የከተማ አስተዳደሩም ይህንን ችግር በመቅረፍ የትምህርት ተሳትፎና ውጤታማነትን ለማሳደግ የቅድመ አንደኛና የመጀመሪያ ደረጃ ተማሪዎችን የትምህርት ቤት ምገባ መርኃ ግብርን ከ2012 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ በማድረግ የመጪው ትውልድ ግንባታ ላይ እየሰራ ይገኛል፡፡ 

የዝግጅት ክፍላችንም ተማሪዎች በትምህርት ቤት ምገባ መርኃ ግብሩ ላይ የተመጣጠነ ምግብ መመገባቸው ጤናማ፣ ንቁ እና ጠንካራ ከመሆን ባሻገር የትምህርት አቀባበላቸው ላይ ምን ውጤት እያመጣ እንደሚገኝ በተለያዩ ትምህርት ቤቶች ቅኝት አድርጓል፡፡ 

ቅኝት ካደረግንባቸው ትምህርት ቤቶች መካከል የካራማራ ሌተናል ኮሎኔል አብዲሳ አጋ እና ቀበሌ 37 ቅድመ አንደኛ፣ አንደኛና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አንዱ ነው፡፡ በትምህርት ቤቱ የ8ኛ ክፍል ተማሪ የሆነችው ቅድስት ውድማጣስ የትምህርት ቤት ምገባ ከመጀመሩ በፊት ቁርሷን ሳትመገብ ወደ ትምህርት ቤት ትሄድ እንደነበር ታስታውሳለች፡፡ በዚህም “አቅም አንሶኝ ወድቄ አውቃለሁ፤ ክፍል ውስጥም ስመለስ ስለምመገበው እንጂ ስለትምህርት ምንም ዓይነት ትኩረት ሰጥቼ አላውቅም፡፡” ስትል ምግብ ሳይመገቡ ትምህርትን መከታተል ምን ያህል  ፈታኝ እንደሆነ ትናገራለች፡፡

“ምገባ ከተጀመረ በኋላ ከቤቴ ስወጣ ‘ምሳ ምን ይቋጠርልኛል’ ብዬ ሳልጨነቅ ትምህርት ቤት ቁርሴንም ምሳዬንም እየተመገብኩ ነው፡፡ የተመጣጠነ ምግብም እያገኘሁ ነው፡፡ አሁን ትኩረቴ ትምህርቴ ላይ ብቻ ሆኗል፡፡ በዚህም አማካኝነት  በክፍል ውስጥ ደረጃዬን አሻሽያለሁ፡፡ በዚህ ዓመት ደግሞ በተለየ ሁኔታ ከዚህ በፊት ያልነበሩ ፍራፍሬ፣ እንቁላል እና የመሳሰሉ የምግብ አይነቶችን እንድንመገብ ተደርጓል፡፡” ስትልም ሀሳቧን አጋርታለች፡፡

በመንግስት ትምህርት ቤቶች ምገባ ከመጀመሩ በፊት የተማሪዎች የትምህርት አቀባበል አጥጋቢ እንዳልነበረ የሚናገሩት ደግሞ በትምህርት ቤቱ የቋንቋ መምህር የሆኑት እንግዳወርቅ በቀለ ናቸው፡፡ 

በአሁኑ ወቅት ሁሉም ተማሪዎች የምገባው ተጠቃሚ መሆናቸው በሰዓቱ ትምህርት ገበታቸው ላይ እንዲገኙ፣ በክፍል ውስጥ ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርጉና ትኩረታቸው ትምህርታቸው ላይ እንዲሆን እድል ፈጥሯል፡፡ ምገባው  የተመጣጠነ ምግብን ጭምር ያካተተ መሆኑ ደግሞ የአዕምሮ እድገትን በማፋጠን የትምህርት አቀባበላቸው የተሻለ እንዲሆን ማድረጉን ከበፊቱ ጋር እያነፃፀሩ ገልፀውልናል፡፡

በትምህርት ቤቱ የምግብ ጥራትና ቁጥጥር ባለሙያ የሆኑት አቶ አወቀ ደምሴም የመምህሩን ሀሳብ ያጠናክራሉ። በምገባ መርኃ ግብሩ የተካተቱት የተመጣጠኑ፣ ገንቢ፣ ሃይልና ሙቀት ሰጪ፣ በሽታ ተከላካይ እና ማዕድናትን የያዙ ምግቦች  ናቸው፡፡ ተማሪዎች የተመጣጠነ ምግብ መመገባቸው  ለአካላዊና አዕምሯዊ ዕድገታቸው  ከመርዳቱ በተጨማሪ በሽታ የመከላከልና የመቋቋም አቅምን የሚፈጥር በመሆኑ በንቃትና በደስታ ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ እያገዘ እንደሚገኝ አብራርተዋል፡፡

የተማሪዎች የተመጣጠነ ምግብ አለማግኘት በአካል ብቻ ሳይሆን በአዕምሮም መቀንጨር ያስከትላል። በትምህርታቸው ውጤታማ የመሆን እድላቸው ዝቅተኛ እንዲሆን ያደርገዋል ያሉት አቶ አወቀ፤ በትምህርት ቤቱ በ2018 የተዘጋጀው የምግብ ዝርዝር (ሜኑ) ልዩ ፍላጎትን ጨምሮ ለእድገታቸው ወሳኝ የሆኑና በንጥረ ነገር ይዘታቸው የተሟሉ ምግቦችን ያካተቱ ናቸው፡፡ ከሂደቱ ጀምሮ በምግብ ዝርዝሩ (ሜኑ) መሰረት ተዘጋጅቶ ተማሪው ጋር እንዲደርስ የቁጥጥርና የክትትል ስራም እየተከናወነ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡

ምገባው ተማሪዎች በሰዓት ተገኝተው ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ እና ውጤታማ እንዲሆኑ ያደረገ መሆኑን የሚገልጹት የካራማራ ሌተናል ኮሎኔል አብዲሳ አጋ እና ቀበሌ 37 ቅድመ አንደኛ፣ አንደኛና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር ዘላለም ተስፋዬ በበኩላቸው፤  ለዚህ በማሳያነት የሚያነሱት በ2017 ዓ.ም የትምህርት ዘመን የ8ኛ ክፍል የትምህርት ቤቱ ተማሪዎች ሙሉ በሙሉ ወደ 9ኛ ክፍል ማለፋቸውን ነው፡፡

በትምህርት ቤቱ የተመጣጠነ ምግብ ለተማሪዎቹ በወጣው የምግብ ዝርዝር፣ በንፅህና እና በጥራት እንዲቀርብ የስነ ምግብ ባለሙያ በመቅጠር እንዲሁም ከትምህርት ቤቱ ሰራተኞች ኮሚቴ በማዋቀር የድጋፍ፣ የቁጥጥር እና ክትትል ስራ እንደሚሰራ ነግረውናል፡፡

መንግስት የተመጣጠነ ምግብ ማቅረብ መቻሉና የትምህርት ቁሳቁስ ማሟላቱ በትምህርት አቀባበላቸው ላይ ከሚያሳድረው በጎ ተፅዕኖ በተጨማሪ ሀገር ወዳድ ትውልድም ለማፍራት ትልቅ ድርሻ እንዳለው ርዕሰ መምህሩ አያይዘው አንስተዋል፡፡

ሌላኛው ቅኝት ያደረግንበት ትምህርት ቤት በመሃል ግንፍሌ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ነው፡፡ በትምህርት ቤቱ የ6ኛ ክፍል ተማሪው ሳምሶን ዮሐንስ በምገባ መርኃ ግብሩ ደስተኛ እንደሆነ ይናገራል፡፡ “የሚሰጠንን የክፍል ስራ እሰራለሁ፤ በክፍል ውስጥም ተሳትፎ አደርጋለሁ፤ ትምህርት ቤት አላረፍድም። የምንመገባቸው ምግቦች አንዳንድ ጊዜ ቤታችን ውስጥ የማይሟሉልን ጭምር ናቸው፡፡ ይህ መሆኑ ደግሞ ትምህርታችንን በንቃት እንድንከታተል አድርጎናል” ሲል ምገባው ምን ያህል ትምህርቱን በአግባቡ ለመከታተል እንዳገዘው ያስረዳል፡፡

መምህርት ፀደይ ሃይሉም የምገባ መርኃ ግብሩ ከመጀመሩ በፊት ቀላል የማይባል ቁጥር ያላቸው ተማሪዎች ቁርስም ሳይመገቡ፤ ምሳም ሳይቋጥሩ ወደ ትምህርት ቤቱ ይመጡ እንደነበር ይናገራሉ፡፡ ይህም ክፍል ውስጥ ራሳቸውን ስተው የመውደቅና ደስተኛ ያለመሆን ችግሮችን ሲያስከትል ቆይቷል። ምገባው ከተጀመረበት ወቅት አንስቶ ደስተኛ ሆነው እንዲማሩ፣ ትኩረት ሰጥተው እንዲከታተሉና በትምህርታቸው ውጤታማ እንዲሆኑ ትልቁን አስተዋጽኦ አድርጎል ይላሉ፡፡

ዝቅተኛ የኢኮኖሚ አቅም ያላቸው ወላጆች ለልጆቻቸው ምግብ ማቅረብ የሚቸገሩ ሲሆን ልጆች በትምህርት ቤት የተመጣጠነ ምግብ ማግኘታቸው አዕምሯቸውና ሃሳባቸው ትምህርታቸው እንዲሆን ያደርጋል፡፡ ይህም የትምህርት አቀባበላቸው የተሻለ እንዲሆን ያደረገና ወላጆች ‘ለልጆቼ ምሳ ምን ልስራላቸው’ ከሚል ጭንቀት የገላገለ፣ በደስታ ወደ ትምህርት ቤት የሚልኩበትን እድል ያመቻቸ መሆኑን ገልፀውልናል፡፡ 

በትምህርት ቤቱ መጋቢ እናት የሆኑት ወይዘሮ ፈትለወርቅ ጥዑመልሳን መንግስት ባዘጋጀው የምግብ ዝርዝር መሰረት ለተማሪዎቹ ምግብ የማዘጋጀት ስራ ይሰራሉ፡፡ ከዚህ በፊት ተማሪዎቹ ባዶ ምሳ እቃ እና ምንም ሳይመገቡ ይመጡ እንደነበር የሚያስታውሱት ወይዘሮ ፈትለወርቅ፣ ምገባ ከተጀመረ በኋላ በተለየ ሁኔታ ምግቡ የተመጣጠነ መሆኑ እና የአዕምሮ እድገት ውስንነት ላለባቸው ተማሪዎች ደግሞ ወተት፣ እንቁላል፣ ስጋ እና ሙዝ እንዲመገቡ በምግብ ዝርዝሩ ውስጥ መካተቱ እንደ እናት እንደሚያስደስታቸው ተናግረዋል፡፡

ለቁርስ ጨጨብሳ፣ ቅንጬ፣ ሳንዱች እና ዳቦ በእንቁላል ቅቅል የሚዘጋጅላቸው ሲሆን፣  ለምሳ ደግሞ  ምስር፣ ሽሮ፣ አትክልት እና ሩዝ የምግብ አይነቶች ይቀርብላቸዋል፡፡ ተማሪዎች ምግብ ሲቀርብላቸው ለመመገብ እንደሚደሰቱት ሁሉ ትምህርታቸውንም ደስ ብሏቸው እንዲከታተሉ ያደርጋቸዋል፡፡ ይህ ደግሞ ለውጤት እንዲበቁ ያግዛቸዋል ሲሉም ገልጸዋል፡፡

የትምህርት ቤቱ ርዕሰ መምህር የሆኑት ዱጋሳ ባይሳም ምገባው በተማሪዎች የትምህርት አቀባበል ላይ አዎንታዊ አስተዋፅኦ እያበረከተ እንደሚገኝ አብራርተዋል፡፡ ሳይመገብ እና የተመጣጠነ ምግብ ሳያገኝ ወደ ክፍል የሚገባ ተማሪ፤ የተሻለ ምግብ ከሚያገኘው ጋር ተመሳሳይ የትምህርት አቀባበል አይኖረውም ያሉት ርዕሰ መምህሩ፤ ምገባው ተማሪዎች ትምህርታቸውን በትኩረት እንዲከታተሉ በማድረግ ከበፊቱ በተሻለ ውጤታማ እንዳደረጋቸው ተናግረዋል፡፡ 

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምገባ ኤጀንሲ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ስንታየሁ ማሞ በበኩላቸው፤ የከተማ አስተዳደሩ ከሚሰራቸው ሰው ተኮር ስራዎች መካከል ከቅድመ መደበኛ እስከ 8ኛ ክፍል ላሉ ተማሪዎች የሚካሄደው የምገባና የቁሳቁስ አቅርቦት አንዱና ዋነኛው ነው፡፡ ይህ ተግባር ከስድስት ዓመት በላይ የሆነው ሲሆን ከዓመት ዓመትም የምገባ ተጠቃሚ የሚሆኑ ተማሪዎችን ቁጥር በማሳደግ እና የምገባ የአሰራር ስርዓቱን በማሻሻል እየተሰራ ነው፡፡

በ2012 ዓ.ም 375 ሺህ 93፣ በ2013 ዓ.ም 527 ሺህ 971፣ በ2014 ዓ.ም 624 ሺህ 272፣ በ2015 ዓ.ም 701 ሺህ፣ በ2016 ዓ.ም 779 ሺህ 231 እና  በ2017 ዓ.ም 840 ሺህ 585 የሚሆኑ በአዲስ አበባ እና ሸገር ከተማ ከቅደመ አንደኛ ጀምሮ እስከ ስምንተኛ ክፍል ድረስ ያሉ በመንግስት ትምህርት ቤቶች የሚማሩ ተማሪዎች የምገባ አገልግሎት ተጠቃሚ ሆነዋል። በ2018 ዓ.ም ደግሞ 976 ሺህ 702 ለሚሆኑ ተማሪዎች በቀን ሁለት ጊዜ የምገባ አገልግሎት ተጠቃሚ ለማድረግ ታቅዶ እየተሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

“ከመመገብ ባሻገር” በሚል መሪ ሀሳብ እየተከናወነ ያለው የተማሪዎች የምገባ መርኃ ግብር ተማሪዎች ትኩረታቸውን ትምህርታቸው ላይ ብቻ እንዲያደርጉ ከማድረግ ባሻገር አዕምሯዊና አካላዊ እድገታቸው የተሻለ እንዲሆን አዎንታዊ አስተዋፅኦ እያበረከተ ነው፡፡ የተመጣጠነ ምግብ እንዲያገኙም ምገባው ከተጀመረ አንስቶ ስድስት የምግብ አይነት በማካተትና በየዓመቱ የምግብ ዝርዝር ማሻሻያዎችን በማድረግ እየተሰራ መሆኑን ወይዘሮ ስንታየሁ ያስረዳሉ፡፡

የምግብ ዝርዝር ማሻሻያ በማድረግ የተመጣጠነ ምግብ እንዲያገኙ በመሰራቱ የተማሪዎች መጠነ ማርፈድና ማቋረጥ በእጅጉ እየቀነሰ እና ውጤታቸውም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ መጥቷል፡፡ ለዚህም የ6ኛ ክፍል ከተማ አቀፍ ፈተና የወሰዱ 94 ከመቶ እና 8ኛ ክፍል ደግሞ 88 ከመቶ ተማሪዎች ወደ ቀጣዩ ክፍል ማለፍ መቻላቸውን ለማሳያነት አንስተዋል፡፡

ወይዘሮ ስንታየሁ እንደነገሩን፤ በትምህርት ቤቶች የቅድመ አንደኛ፣ ከ1ኛ እስከ 8ኛ ክፍል እና የልዩ ፍላጎት ተማሪዎችን ማዕከል ያደረጉ ሶስት አይነት የምግብ ዝርዝሮች (ሜኑ) ይዘጋጃሉ። 1 ሺህ 269 የአንደኛ ደረጃ ተማሪዎች የአዕምሮ እድገት ውስንነት ያለባቸው ሲሆን እነዚህን ያማከለ እንደ እንቁላል፣ ሙዝ እና ቅንጬ የመሳሰሉ የምግብ አይነቶችን በማካተት የምግብ ዝርዝሩን በማዘጋጀት እየቀረበላቸው ይገኛል፡፡

ለአንድ ሀገር እድገትና ለውጥ መሰረቱ ትምህርት መሆኑን የሚናገሩት ምክትል ዋና ዳይሬክተሯ፤ ምገባው ተማሪዎች የተሻለ የትምህርት አቀባበል እንዲኖራቸውና ውጤታማ እንዲሆኑ የሚያደርግና በትውልድ ግንባታ ላይ የሚውል መዋዕለ ንዋይ ነው፡፡ ወደፊትም ተማሪዎች በተማሩት ትምህርት ውጤታማ እንዲሆኑ የክትትልና ቁጥጥር ስራ፣ የመጋቢ እናቶችንም ማገዝ እና በተማሪዎች የትምህርት አቀባበል ላይ እየመጣ ያለውን ለውጥ በየጊዜው ክትትል የማድረግ ስራዎችና ማሻሻያ የማድረግ ተግባራት እንደሚከናወኑ ጠቁመዋል፡፡

በፋንታነሽ ተፈራ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review