የሆረ ሃርሰዴ ኢሬቻ በዓል አብሮነትና ብዝሀነት ጎልቶ የታየበት መሆኑን ከተለያዩ ክልሎች በመምጣት በበአሉ ላይ የታደሙ ተሳታፊዎች ገልጸዋል።
ኢሬቻ የክረምት ወራት መጠናቀቅና የጸደይ ወራት ብራ መምጣትን ተከትሎ በየ አመቱ የሚከበር በአል ነዉ፡፡
የኦሮሞ ህዝብ ከሌሎች ብሄር ብሄረሰቦች ጋር በአብሮነትና በአንድነት የሚያከብረዉ በመሆኑ ኢሬቻ የወንድማማችነት መገለጫ መሆኑ በብዙዎች ዘንድ ይታመንበታል፡፡
የኢሬቻ በአል ኦሮሚያን ጨምሮ በተለያዩ የሃገሪቱና የአለም ክፍሎች የሚከበር ሲሆን የዘንድሮዉ የኢሬቻ በአልም በሆረ ፊንፌኔና በሆረ-ሀርሰዴ ባህላዊ እሴቱን በጠበቀ መንገድ በድምቀት ተከብሯል፡፡

በአከባበር ሥነ ሥርዓቱ ላይ የኦሮሞ ብሔር ተወላጆችና ብሔር ብሔረሰቦችን ጨምሮ ከተለያዩ የአለም ክፍሎች የመጡ ቱሪስቶች ተሳትፈዉበታል፡፡
ከማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጉራጌ ዞን የመጡት ወ/ሮ ሀያት ዘውዱ ከእነቤተሰቦቿ በበአሉ ላይ መታደማቸዉን በመግለጽ በዓሉ ትውፊቱን፣ እሴቱን፣ አሳታፊነቱን ጠብቆ ወደ ትውልድ እንዲተላለፍ ብዝሀነትን አስጠብቆ እንዲጓዝ የበኩሏን እንደምታበረክት ተናግራለች።
ከአዳሚ ቱሉ ጁዶ ኮምቦልቻ በበአሉ ላይ የታደመዉ ወጣት ኦስማን ገንዳዴ በበኩሉ በአሉ ባህላዊ ህሴቱን በጠበቀ መንገድ በስኬትና በድምቀት መከበሩን ተናግሯል፡፡
ሌሎች የበዓሉ ታዳሚዎችም ኢሬቻ የመሻገር፤ የይቅርታ እና የምስጋና እሴቶች የተንጸባረቁበት መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በአሉ ለኢትዮጵያ ማንሰራራት ትልቅ መሰረት የጣለ መሆኑንም ለአዲስ ሚዲያ ኔትወርክ ተናግረዋል፡፡
በአለኸኝ አዘነ