ኢትዮጵያን ጨምሮ ከሰሀራ በታች በሚገኙ የአፍሪካ ሀገራት የዋጋ ንረት እና የገንዘብ ገበያ በመረጋጋት ላይ እንደሚገኝ የዓለም ባንክ አዲስ ባወጣው ሪፖርቱ ጠቁሟል።
ሪፖርቱ ቀጠናው በ2025 3.8 በመቶ እድገት እንደሚያስመዘግብ ያስቀመጠ ሲሆን፤ ይህም በአመቱ መጀመሪያ ላይ ከተተነበየው የ3.5 በመቶ ኢኮኖሚያዊ እድገት ብልጫ የታየበት ነው።
የቀጠናው አጠቃላይ ኢኮኖሚያዊ እድገት በሚቀጥሉት ሁለት አመታት እስከ 4.4 በመቶ እደገት እንደሚያስመዘግብም ሪፖርቱ ጠቁሟል።
በቀጣናው ትልቅ ኢኮኖሚ ያላቸው ኢትዮጵያ፣ ናይጄሪያ እና ኮትዲቫር አወንታዊ እድገት እያስመዘገቡ እንደሚገኙ ሪፖርቱ አመላክቷል።
የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ በትላንትናው እለት በነበረው የጋራ ምክርቤት መክፈቻ የመንግሥትን የ2018 በጀት አመት የትኩረት አቅጣጫዎች ባቀረቡበት ወቅት፤ የዋጋ ንረት በ2016 አመት ከነበረበት 19.9 በመቶ በ2017 ወደ 13.9 በመቶ መቀነሱን መናገራቸው ይታወሳል ።
በተጨማሪም የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በ2017 በጀት ዓመት 9 ነጥብ 2 በመቶ እድገት ማስመዝገቡን እና ኢትዮጵያ በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ ከወጪ ንግድ 8 ነጥብ 3 ቢሊየን ዶላር ማግኘቷን አብራርተዋል ።
የዓለም ባንክ ሪፖርት ከሰሀራ በታች በሚገኙ የአፍሪካ ሀገራት እየታየ ለሚገኘው የኢኮኖሚ ሁኔታ የተረጋጋ የገንዘብ ምንዛሪ ምጣኔ እና የኢንቨስትመንት ማደግ ዋነኛ ምክንያት መሆናቸውን አስቀምጧል።
የባንኩ የአፍሪካ ቺፍ ኢኮኖሚስት አንድሪው ዳባሊን፣ በቅርብ አመታት የገንዘብ የመግዛት አቅም ከአሜሪካ ዶላር ጋር ሲወዳደር ከፍተኛ ቅናሽ አስመዝግበው የነበሩ ሀገራት አሁን ላይ የተረጋጋ የገንዘብ ግብይት እና የውጭ ምንዛሪ ግብይት እየተስተዋለባቸው ነው ብለዋል።
ከአስርት አመታት የውጭ እዳ ጫና ተጽዕኖ፣ ከዓለም አቀፍ የምርት መስተጓጐል እና ከሀገር ውስጥ ምርታማነት መዳከም እያገገመ የሚገኘውን ምጣኔ ሀብት እድገት ለማስቀጠል አሁንም ተጨማሪ ስራዎች እንደሚጠበቁ ኢኮኖሚስቱ አሳስበዋል።
ይህም እያደገ ለሚገኘው የወጣት ሀይል የስራ እድል ፈጠራን በማጠናከር የሚጀመር ነው ተብሏል።
በአፍሪካ ሶስት አራተኛ የስራ እድል በኢመደበኛ ዘርፍ ላይ የተመረኮዘ መሆኑን ተከትሎ፤ በቀጠናው እንዲሁም በአህጉር ደረጃ አነስተኛ እና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞችን አቅም ማጎልበት ለስራ እድል ፈጠራ እንዲሁም ለኢኮኖሚያዊ እድገት ሁነኛ መፍትሔ ሆኖ ተቀምጧል።
ባንኩ በሪፖርቱ ማጠቃለያ ዓለም አቀፋዊ ሁኔታ እና አሁንም ከዋነኛ ኢኮኖሚያዊ ተግዳሮትነት ያልተላቀቀው የውጭ እዳ ጫና ተጽዕኖ ለአህጉሪቱ ምጣኔ ሀብት እድገት ማነቆ ሆኖ እንደሚቀጥል አሳስቧል።
በዳዊት በሪሁን