በአዲስ አበባ ከተማ በጭር ጊዜ ዉስጥ ያየነዉን ተዓምራዊ ልማትና እድገት በሌሎች የአዉሮፓና አሜሪካ ሃገራት የሚኖሩ ቱሪስቶች መጥተዉ እንዲጎበኙ የበኩላችንን እንወጣለን ሲሉ በሆረ ፊንፊኔ የኢሬቻ በአል ላይ የታደሙ ትዉልደ ኢትዮጵያዊያን ገልጸዋል፡፡
ኑሮዋ በዩኤስ ኤ ኮሎራዶ ያደረገችው ትውልደ ኢትዮጵያዊቷ ከ15 አመታት የውጪ ሀገር ቆይታ በኋላ ነው በሆራ ፊንፊኔ የኢሬቻ በዓል ላይ ለመታደም ወደ ሀገሯ የገባችው፡፡ ወጣቷ የትዳር አጋሯን እና ሁለት ልጆቻን በመያዝ በዓሉን ለመታደም መምጣቷን ለኤ ኤም ኤን ተናግራለች፡፡

ከ15 አመታት በፊት የምታውቃትን አዲስ አበባ አሁን አደናግራታለች፡፡ አዲስ አበባ ፍጹም በሚባል ደረጃ ተቀይራለች በዚህም ደስተኛ ነኝ ትላለች፡፡
ከ15 አመት የኮሎራዶ ቆይታ በኋላ ወደ ሀገሯ ለመምጣት ምክንያት የሆናት ደግሞ ልጆቿ ሀገራቸውን እና የሀገራቸውን ባህልና ወግ እንዲያቁ በማሰብ መሆኑን ነው የገለፀችው ፡፡

ባህሌን፣ ሀገሬን እና ህዝቦቿን በማየቴ እጅግ በጣም ደስትኛ ነኝ የምትለው የቤተሰብ አባል ባየችው ልማትና ለዉጥ እጅግ ተደምማለች፡፡
በዓሉን የሚያከብሩት በጋራ ነው ይህ ደግሞ እጅግ ደስታን ፈጥሮልኛል፤ የመዲናዋ ልማትና ሰላም በጣም ቆንጆ ነው፤ ቆንጆ ነገር ማየት ደግሞ ደስታን ይፈጥራል ነው ያለችው፡፡
ኦላ የኢሬቻ በዓል ለመታደም ከአየርላድ ከጓደኞቿ ጋር ሆረ ፊንፊኔ ለመታደም እንደመጣች ነው ለኤ ኤም ኤን የገለፀችው የመምጣቷ ምክኒያት ደግሞ ፣ የባለቤቷ እና ቤተሰቦቿ እና ጓደኞቿ፣ አዲስ አበባ መምጣት አለብሽ ውትወታ መሆኑን ነው ያጫወተችን ፡፡

አዲስ አበባ በጣም የምታምር እና ድንቅ ከተማ ሆና እንዳገኘቻት የተናግረችው ኦላ የበዓሉ ድባብ፣ የህዝቡ ወንድማማችነት፣ የከተማዋ ልማት ድምቀት ልዩ ነውም ብላለች ። አዲስ አበባ በአጭር ጊዜ ዉስጥ ዘመናዊ ከተማ ሆናለች ስትል ገልጻለች።
ኦላ በመምጣቷም እጅግ ደስተኛ መሆኗን እና ክብርም እንደተሰማት ገልፃ ፣ የህዝቡ እንግዳ ተቀባይነት፣ መስተንግዶ፣ ባህሉ እና አለባበሱም ዉበትን ገላጭ ሆኖ አግኝቼዋለሁ ብላለች ።

ይህን እኔ እና ጓደኞቼ ያየነውን ተዓምር እና አስደማሚ ከተማ ሌሎችም ቱሪስቶች፣ በአውሮፓ፣ በኢሲያ ፣ በአሜሪካ እና በተለያዩ ሃገር የሚኖሩ ዜጎች ይህችን ዉብ ከተማ እና ግሩም ህዝብ መጥተው እንዲጎበኙት እጋብዛቸዋለሁም፣ ኢትዮጵያ ዉብ ሃገር ናትም ብላለች ።
የኦላ ባለቤት በበኩሉ እዚህ መገኘት እጅግ ደህንነት እና ምቾት እንዲሰማህ ያደርጋል። ለሚቀጥለው አመትም በርግጠኝነት ይህንን ድንቅ ባህል ያለውን ህዝብ እና የኢሬቻ በዓልን እንደምታደም እርግጠኛ ነኝ ነው ያለው ።
በበረከት ጌታቸው