የህንድ አለም አቀፍ የቡና ገበያ ከኢትዮጰያ ከፍተኛ ፉክክር እያጋጠመው እንደሚገኘ ተዘገበ

You are currently viewing የህንድ አለም አቀፍ የቡና ገበያ ከኢትዮጰያ ከፍተኛ ፉክክር እያጋጠመው እንደሚገኘ ተዘገበ

AMN – መስከረም 28/2018 ዓ.ም

የኢትዮጵያ እና የኡጋንዳ ቡና በአለም አቀፍ ደረጃ የህንድን የቡና ገበያ ድርሻ እየተፎካከረ እንደሚገኝ ተዘግቧል።

“ሮበስታ” የተባለውን እና ከፍተኛ የካፊን መጠን የሚይዘውን የቡና ዝርያ በማቅረብ በአለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነትን ያገኙት የህንድ ቡና ነጋዴዎች፤ ቡና አብቃይ ከሆኑት ኢትዮጵያ እና ኡጋንዳ ከፍተኛ ውድድርን እየተጋፈጡ እንደሚገኙ ቢዝነስ ላይን የተባለው የህንድ ጋዜጣ ዘግቧል።

በለንደን አለም አቀፍ ቡና ገበያ ላይ የህንዱ ሮበስታ ቡና ከኢትዮጵያ እና ኡጋንዳ ከሚመጡ ቡናዎች ጋር የነበረው የዋጋ ልዩነት በቶን 500 ዶላር እና ከዛ በላይ አንደነበር ዘገባው ይጠቅሳል።

የሀገሪቱ የቡና ላኪዎች ማህበር ፕሬዝዳንት ራሚሽ ራጃህ ሁለቱ ሀገራት የሚያቀርቡት የቡና ምርት መጠን ማደግ እና የዋጋቸው ቅናሽ መሆን ተመራጭ እንዲሆኑ እንዳደረጋቸው ለጋዜጣው ተናግረዋል።

በአውሮፓ የኡጋንዳ በመካከለኛው ምስራቅ ደግሞ ኢትዮጵያ ቡና የህንድ ነጋዴዎችን ከጨዋታ ውጭ እያደረገ ይገኛል ሲሉም ፕሬዝዳንቱ አክለዋል።

ሮበስታ የተባለው የቡና ዝርያ በማዕዛው እና በካፊን ደረጃው ጥንካሬ በአለም ላይ ተፈላጊ በመሆኑ የወጣላት ዋጋም ከፍተኛ ነው።

አረቢካ ቡናን የምታቀርበው ኢትዮጵያ ደግሞ ይህን የቡና ዝርያ ለመፎካከር እና ወደ ገበያው ዘልቆ ለመግባት የዋጋ ልዩነትን እንደ ገበያ ስትራቴጂ እየተጠቀመች እንደምትገኘ ጋዜጣው በዘገባው አካቷል።

ህንድ በአውሮፓ 5ተኛዋ ከፍተኛ ቡና ላኪ ሀገር ስትሆን ከ55-60 በመቶ የሀገሪቱ ቡና የሚላከውም ወደዚሁ ቀጠና እንደሆነ መረጃዎች ይጠቁማሉ።

በዚህ አካባቢ የኡጋንዳ ቡና በዋጋው ምክንያት ተፈላጊ ሆኗል፤ ጣሊያን እና ጀርመንን የመሳሰሉ የህንድ ቡና ቀዳሚ ደንበኞች አሁን ላይ ፊታቸውን ወደ ምስራቅ አፍሪካ እያዞሩ ነው ተብሏል።

በዳዊት በሪሁን

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review