የኢትዮጵያን ብልፅግና እውን ማድረግ የሚያስችል መሰረት እየተጣለ ነው ሲሉ የብልፅግና ፓርቲ የፌዴራል ተቋማት አስተባባሪ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ተስፋዬ ቤልጂጌ(ዶ/ር) ገለጹ።
የኢኮኖሚ ብልፅግና ክላስተር የ2017 በጀት ዓመት የፖለቲካ እና አደረጃጀት ስራዎች አፈጻጸም የወረዳዎች እውቅና አሰጣጥ መርሃ ግብር እየተካሄደ ነው፡፡
የብልፅግና ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልና የፌዴራል ተቋማት አስተባባሪ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ 2018በጀት ዓመት የኢትየጵያን ኢኮኖሚ ወደ ወሳኝ ምዕራፍ የሚያሸጋግር መሰረት የተጣለበት ነው፡፡
የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ መጠናቀቅ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የተበሰረበት መሆኑን አውስተዋል።
ኢትዮጵያ የከርሰ ምድር ሃብቷን አውጥታ መጠቀም የሚያስችሏትን ግዙፍ ፕሮጀክቶች ይፋ ማድረጓን ጠቅሰው፤ ኢትዮጵያ በወሳኝ ምዕራፍ ላይ እንደምትገኝ አብራርተዋል።
ምክትል ሰብሳቢው ተስፋዬ(ዶ/ር) እንደገለጹት፤ የኢትዮጵያን ብልፅግና ማረጋገጥ የሚያስችል መሰረት እየተጣለ ነው ብለዋል፡፡
ብልፅግናን እውን ለማድረግ በሚደረገው እንቅስቃሴ የሚያጋጥሙ ፈተናዎችን ለማለፍ በትኩረት መስራት እንደሚገባ ጠቁመው፤ የመልካም አስተደደር ችግሮች እልባት እንዲያገኙ የሚጠበቅብንን ድርሻ መወጣት አለብን ሲሉ አስገንዝበዋል፡፡
ከአገልግሎት አሰጣጥ አኳያም ከህዝቡ የሚነሱ ጥያቄዎችን በአግባቡ ለመመለስ የተጀመሩ ስራዎችን ማጠናከር እንደሚገባም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
የብልፅግና ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልና የኢኮኖሚ ክላስተር ሰብሳቢ አቶ መላኩ አለበል በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ በአፍሪካ የብልፅግና ተምሳሌት ለመሆን ያስቀመጠችው ግብ በትክክለኛ መስመር ላይ ይገኛል ብለዋል፡፡
የተፈጥሮ ጋዝ፣ የማዳበሪያ ፋብሪካ ፕሮጀክቶችን ጨምሮ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ይፋ የተደረጉ ፕሮጀክቶች ለዚህ ማሳያዎች መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ተቀባይነት እያገኘ መምጣቱን አስታውሰው፤ ይህም የኢትዮጵያ ልዕልና ከፍ እያለ ለመምጣቱ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡
የተገኙ ውጤቶችን ይበልጥ ለማላቅ ርብርብ እንደሚጠይቅ ጠቁመው፤ ሀገራዊ ኢኒሼቲቮች ግባቸውን እንዲመቱ ተሳትፏችን ይበልጥ ሊጎላ ይገባል ማለታቸዉን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
የእውቅና መርሃ ግብሩ በወረዳዎች መካከል በአፈፃፀም ዙሪያ ልምድ ልውውጥ ለማድረግና የላቀ አፈጻጸም ለማስመዝገብ ትልቅ ሚና እንዳለውም ገልጸዋል፡፡