ተመራማሪዎች ኮምፒውተር ማንቀሳቀስ የሚችል የሰው ልጅ አዕምሮ ፈጠሩ

You are currently viewing ተመራማሪዎች ኮምፒውተር ማንቀሳቀስ የሚችል የሰው ልጅ አዕምሮ ፈጠሩ

AMN – መስከረም 29/2018 ዓ.ም

በስዊዘርላንድ የሚገኙ ተመራማሪዎች ህይወት ካላቸው ሴሎች ኮምፒውተር ማንቀሳቀስ የሚችል አነስተኛ አዕምሮ መስራታቸው ተሰምቷል።

ተመራማሪዎቹ ይህን አዕምሮ የፈጠሩት የሰው ልጅ ጭንቅላት ጥቂት የቴክኖሎጂ እገዛ ተደርገውለት ከሰው ሰራሸ አስተውሎት ጋር ያለውን ልዩነት ለማነጻጸር ነው ማለታቸውን ቢቢሲ ዘግቧል።

ንጽጽሩ የሚካሄደው ኤ አይ ነገሮችን የሚማርበት እና መረጃዎችን የሚያሰባስብበትን መንገድ ለማወቅ ነው ተብሏል።

በ”ኦርጋኖይድ ክላስተር” የሚመረቱት የአዕምሮ ነርቮችን በቤተ ሙከራ በማበልጸግ በጥቂት ጊዜዎች ውስጥ በትናንሽ ኮምፒውተሮች ላይ ተገጥመው አገልግሎት እንዲሰጡ እንደሚደረግም ተመራማሪዎቹ ተናግረዋል።

ከጥናቱ ተመራማሪዎች መካከል አንዱ የሆኑት ዶክተር ፍሬድ ጆርዳን ቴክኖሎጂው ውስብስብ ከሆነው የሰው ልጅ የአዕምሮ አሰራር ጋር ሊስተካከል ባይችልም የሚደረጉ ሙከራዎች እና ምርምሮች በዛ ደረጃ ላይ ለመድረስ አላማ ያነገቡ መሆናቸውን ይናገራሉ።

በአሁኑ ወቅት በሚገኘው የምርምር ደረጃ በትናንሽ ኮምፒውተሮች ላይ የተገጠሙ ሰው ሰራሽ አዕምሮዎች በኪቦርድ ለሚሰጣቸው ትዕዛዞች ምላሽ መስጠት መቻላቸው ተገልጿል።

ይህ ማለት ኤሌክትሪካል መልዕክቶችን እና ትዕዛዞችን መቀበል እንዲሁም መመዝገብ በሚያስችል ቁመና ላይ ይገኛሉ እንደማለት ነው።

ኦርጋኖይድ ሴሎቹ የደም ስር አልባ በመሆናቸው የሚያንቀሳቅሳቸው ሀይል ያስፈልጋቸዋል ይህንን አማራጭ አፈላልጎ ማግኘት የተመራማሪዎቹ ቀጣይ የቤት ስራ ነው ተብሏል።

ከስዊዘርላንድ ባለፈ በሌሎች ሀገራት ሰው ሰራሽ አዕምሮዎችን ኮምፒውተር ላይ ለመጠቀም የሚደረግ ምርምር በሰፊው እየተካሄደ ነው።

ለአብነት በአሜሪካ የሚገኘው የጆን ሆብኪንስ ዩኒቨርስቲ ለአልዛይመር እና ለአዕምሮ እድገት ውስንነት ጥናት ላይ የሚውሉ ኮምፒውተሮች ላይ ሰው ሰራሽ አዕምሮዎችን ጥቅም ላይ በማዋል ላይ ይገኛል።

በዳዊት በሪሁን

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review