በርካታ የሚሊየን ዶላር ባለሀብቶች የሚገኙባቸው የአፍሪካ ሀገራት

You are currently viewing በርካታ የሚሊየን ዶላር ባለሀብቶች የሚገኙባቸው የአፍሪካ ሀገራት

AMN – መስከረም 29/2018 ዓ.ም

በአፍሪካ አህጉር የግል ባለሀብቶች እድገት እና ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ በከፍተኛ መጠን እያደገ ይገኛል።

አፍሪካ ዌልዝ ሪፖርት በ2025 ሪፖርቱ ምንም እንኳን አሁንም በአህጉሪቷ ፍትሀዊ የሀብት ክፍፍል በተገቢው መንገድ ባይሰፍንም በሚሊየን ዶላር የሚገመት ሀብት ያካባቱ ዜጎች ቁጥር እየጨመረ ይገኛል ብሏል። በመጪዎቹ አስርተ አመታት በአህጉሪቷ አንድ ሚሊየን ዶላር እና ከዛ በላይ ሀብት ያካበቱ ዜጎች መጠን በ65 በመቶ እንደሚያድግ አስቀምጧል።

ይህም አህጉሩን የሀብት ምንጨ መገኛ ወደ መሆን የሚያሸጋግረው ነው ተብሏል። በ2050፤ 29 ትሪሊየን ዶላር እንደሚያመነጭ ኢኮኖሚ እና የህዝብ ቁጥሯ 1.5 ቢሊየን ይደርሳል የተባለችው አፍሪካ ከእስያ እና ከመካከለኛው ምስራቅ ቀጠና በተሻለ በርካታ ሚሊየነሮችን እያፈራች እንደምትገኘ ሪፖርቱ ጠቅሷል።

ደቡብ አፍሪካ ባለፉት አስርተ አመታት በደካማ የኢኮኖሚ እድገት እና የፖሊሲ መዋዠቅ ምክንያት የሚሊየነሮቿ ቁጥር በ6 በመቶ ቅናሸ ቢያሳይም ከ41 ሺህ በላይ ሚሊየነሮችን በመያዝ ከአህጉሩ ቀዳሚ ሆና ቀጥላለች። የገንዘብ የመግዛት አቅም መዳከም እና መዋቅራዊ የኢኮኖሚ ችግር ያጋጠማት ግብጽ በተመሳሳይ ባለፉት አስር አመታት የ15 በመቶ ቅናሽን ብታስተናግድም 14 ሺህ 800 ሚሊየነሮችን ይዛለች።

በአንጻሩ 7500 ሚሊየነሮች ያሉባት ሞሮኮ የ40 በመቶ ጭማሪን አስመዝግባለች ። በምስራቅ አፍሪካ ኬኒያ እና ኢትዮጵያ ከቅርብ አመታት ወዲህ ቀጣይነት ያለው የሚሊየን ዶላር ባለሀብቶች ቁጥር እያደገ የሚገኝባቸው ሀገራት ሆነው ተቀምጠዋል።

የቀጠናው የፋይናንስ ማዕከል ተብላ የምትጠራው ናይሮቢ 6800 ሚሊየነሮች የሚገኙባት ሲሆን፤ ሰፊ የከተሞች እድገት እና ኢንቨስትመነት መጨመርን ያስመዘገበችው ኢትዮጵያ በበኩሏ የ30 በመቶ ጭማሪ በማስመዝገብ 2400 ሚሊየነሮች መገኛ ነች ተብሏል።

በዳዊት በሪሁን

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review