የኢትዮጵያ የባህር በር ፍላጎት ትክክለኛነቱና አግባብነቱ ስለተረጋገጠ በአለም አቀፍ ደረጃ ትኩረት የተሰጠው አጀንዳ ሆናል ሲሉ የህግ ባለሙያ የሆኑት አቶ ማሩ አብዲ ገልፀዋል፡፡
የኢትዮጵያ የባህር በር ፍላጎት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ (ዶ/ር) ሀሳቡን ከገለፁ በኃላ የኢትዮጵያ ህዝብ ሀሳባቸውን ገዝቶታል፤ በአሁኑ ወቅት የባህር በር የሕዝብ አጀንዳ ሆኗል ሲሉ ከኤ.ኤም.ኤን ጋር ቆይታ ያደረጉት አቶ ማሩ አብዲ ተናግረዋል፡፡

አጀንዳው ከኢትዮጵያ ህዝብ ባለፈ በቀጠናው ያሉ ሀገራት እንዲሁም ጉዳዩ የሚመለከታቸው አለም አቀፍ ተቋማት የሚሰጡትን ሀሳብ ደምረን ስናየው የባህር በር ፍላጎቱ አለምአቀፋዊ ድጋፍ እንዳለዉ ማሳያ ነዉ ብለዋል፡፡
የሀገራት መሪዎች፣ አለም አቀፍ ተቋማት፣ እንደ አሜሪካ፣ ፈረንሳይና የአፍሪካ ህብረት የኢትዮጵያ የባህር በር ፍላጎት ህጋዊና ተገቢነት ያለው ጥያቄ መሆኑን ደግፈዋል ነው ያሉት አቶ ማሩ፡፡
አንድ ሀገር የባህር በር ከሌላት የባህር በር ካላቸው ሀገራት ለመጠቀም የሚያስችል ህግ በአለም ሀገራት ተፈርሞ የጸደቀ ህግ መኖሩንም ገልፀው፤ ከአንቀጽ 124 እስከ 139 የባህር ህጎችን በተመለከተ በግልጽ መደንገጉንም ተናግረዋል።

ማንኛውም የባህር በር የሌለው ሀገር በሌሎች የባህር በር በላቸው ሀገራት ውስጥ ታልፎ በእኩልነትና ሉአላዊነትን ሳይፃረር የሚከናወን ነው ሲል ህጉ ይደነግጋላል ብለዋል፡፡
እነዚህ ህጎች የባህር በር የማግኘትንም ሆነ የባህር በር በመጠቀም የመልማትን መብት የሚያረጋግጡ ናቸው ሲሉ ገልፀዋል፡፡
ህዝቡ የሀሳቡን ገዥነት ተቀብሎ ባለቤት እንደሆነ ሁሉ የዓባይ ግድብ ሲገነባ በማህበራዊ ሚዲያ የነበረውን ንቅናቄና ተሣትፎ ለባህር በር ፍላጎቱ መሣካት ሊረባረብ ይገባል ነው ያሉት ።
የባህር በር የሚያስፈልገው ለሀገራት የጋራ ልማት፣ አብሮነት እንዲሁም ለጋራ ሉአላዊነት ነው ያሉቱ አቶ ማሩ፤ ለአጀንዳው መሳካት ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል ፡፡
በ-በረከት ጌታቸው