ኢትዮጵያ በአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና ስምምነት ትግበራ በመታገዝ ምርቶቿን በአየርና በየብስ ትራንስፖርት ወደ የተለያዩ አፍሪካ አገራት መላክ ጀመረች።
በአፍሪካ አህጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጣና የመጀመሪያ ግብይት ማስጀመሪያ መርኃ ግብር ተካሂዷል።
በመርኃ ግብሩ ላይ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊ እና የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ አደም ፋራህ፣ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) ፣ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር አለሙ ስሜ (ዶ/ር)፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰውን ጨምሮ በርካታ የመንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) በዚሁ ጊዜ እንዳሉት፤ አህጉራዊው ነፃ የንግድ ስምምነት የሀገራችንን ንግድ ለማዘመንና ለመላው ዓለም ለመግለጥ የሚያስችል ነው። በተለይ በእቃዎች ዋጋ ተመን (ታሪፍ) ላይ ስምምነት ተደርሶ፣ ዛሬ የመጀመሪያውን ጭነት በአየርና በየብስ መላክ መጀመሩን አብስረዋል።

በስምምነቱ መሰረት የታሪፍ ምጣኔን ዜሮ አድርጎ በሚደረገው ግብይት የሀገራችን የወጪ ንግድ በትክክለኛው መስመርና እድገት ላይ እየመጣ ያለውን ስኬት በማሳለጥ ረገድ ትልቅ ድርሻ ይኖረዋል ነው ያሉት።
አህጉራዊው ነፃ የንግድ ስምምነት በአፍሪካ አገራት መካከል ያለውን የገበያ ትስስር ለማጎልበት ወሳኝ መድረክ ነው ብለዋል። ዛሬ የተጀመረው የመጀመሪያ የወጪ ንግድ በዋነኝነት ትኩረት የሚያደርገው በምስራቅና በደቡብ አፍሪካ ሀገራት ላይ መሆኑን አስታውቀዋል።
በዚህም በመጀመሪያው ጭነት ሥጋ፣ አትክልትና ፍራፍሬ፣ ቀይና ነጭ ቦለቄ እንዲሁም በቆሎ እና ሌሎች ምርትችን ወደ ኬንያ፣ ሶማሊያ እና ደቡብ አፍሪካ በአየር ጭነትና በየብስ ትራንስፖርት መላክ መጀመሩን ነው የተናገሩት።
ትግበራው የሀገራችንን የወጪ ንግድ ሂደት ይበልጥ ለማሳለጥ የሚያስችል መሆኑን መናገራቸዉን ተዘግቧል፡፡