የአፍሪካ አህጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጣናን ሙሉ ለሙሉ ገቢራዊ ማድረግ ጊዜ የማይሰጠው አንገብጋቢ ጉዳይ ነው ሲሉ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር መሐሙድ አሊ ዩሱፍ ገለጹ።
24ኛው የምስራቅና ደቡብ አፍሪካ አገራት የጋራ ገበያ (ኮሜሳ) የመሪዎች ጉባኤ በኬንያ ናይሮቢ እየተካሄደ ነው።
የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር መሐሙድ አሊ ዩሱፍ በጉባኤው ላይ ባደረጉት ንግግር ዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ ሁነቶች በአፍሪካ የኢኮኖሚ እድገት እና ተወዳዳሪነት ተጽእኖ እያሳደሩ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ይህም ከመቼው ጊዜ በላይ የአፍሪካ አህጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጣና ሙሉ ለሙሉ በአፋጣኝ መተግበር እንደሚገባው የሚያመላክት ነው ብለዋል።
ሊቀ መንበሩ የአፍሪካ ቀጣናዊ የኢኮኖሚ ማህበረሰቦች ከቀረጥ ጋር ያልተያያዙ የንግድ ገደቦችን በማንሳት እና በአፍሪካ ሀገራት መካከል የተሳለጠ የንግድ ልውውጥ ማድረግ የሚያስችሉ ማዕቀፎችን በመተግበር ለአጀንዳ 2063 መዋቅራዊ ትራንስፎርሜሽን ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።
የኮሜሳ፣ የደቡብ አፍሪካ የልማት ማህበረሰብ (ሳዴቅ) እና የምስራቅ አፍሪካ ማህበረሰብ (ኢኤሲ) የሶስትዮሽ ትብብር ማዕቀፍ መሆኑን ጠቅሰው፤ ማዕቀፉ የትስስር አጀንዳ ተምሳሌት እና አንድ የሆነች፣ የበለጸገች እና ራሷን የቻለች አህጉር ለመፍጠር የተጀመረውን ጉዞ የተስፋ ብርሃን ፈንጣቂ መሆኑን ተናግረዋል።
የአፍሪካ ህብረት ከቀጣናዊ የኢኮኖሚ ማህበረሰቦች ጋር ጠንካራ ትብብር በመፍጠር ቀጣናዊና አህጉራዊ የትስስር አጀንዳዎችን ትግበራ ለማፋጠን በቁርጠኝነት እንደሚሰራ መግለጻቸውን ኢዜአ ከህብረቱ ያገኘው መረጃ ያመለክታል።