የአሜሪካዉ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የጓጉለትን የኖቤል ሽልማት ቬንዙዌላዊቷ ፖለቲከኛ ማሪያ ኮሪና አሸንፈዋል፡፡
የቬንዚዌላ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪ እና ፖለቲከኛ ማሪያ ኮሪና ማቻዶ የዘንድሮው አመት የኖቤል የሰላም ሽልማት ተመራጭ ሆነዋል።
ግለሰቧ በሀገራቸው ዲሞክራሲያዊ መብቶች እንዲከበሩ እና የዴሞክራሲ ሽግግር እንዲደረግ በሚያደርጉት ትግል ለኖቤል የሰላም ሽልማት መመረጣቸውን የኖርዌይ የኖቤል ኮሚቴ አስታውቋል።
የ58 አመቷ የኢንዱስትሪ መሀንዲስ ማቻዶ ለፕሬዝዳንትነት እንዳይወዳደሩ በ2024 በቬንዙዌላ ፍርድ ቤቶች ታግደዋል።
ነገር ግን ከ2013 ጀምሮ በስልጣን ላይ ያሉትን ፕሬዝዳንት ኒኮላስ ማዱሮን በተለያዩ መንገዶች እየተገዳደሩ ዘልቀዋል።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የዘንድሮው የሰላም ሽልማት ይገባኛል በሚል በተደጋጋሚ ያደረጉትን ንግግር ተከትሎ አሸናፊ ሊሆኑ እንደሚችሉ ሰፊ ግምት አግኝተው ነበር።
ትራምፕ በጋዛ ያለውን ጦርነት ለማቆም ያደረጉት የመጀመሪያ ምዕራፍ ስምምነት ረቡዕ ከመታወጁ በፊት የኖቤል ኮሚቴ የመጨረሻ ውሳኔውን እንዳሳለፈ ሮይተርስ ዘግቧል።
በዳዊት በሪሁን