በኮሜሳ የመሪዎች ጉባኤ ላይ ኢትዮጵያ የዲጂታል መሠረተ ልማት ለሀገር በቀል ኢኮኖሚ ዕድገት ቁልፍ ጉዳይ አድርጋ እየሰራች መሆኑን ማስገንዘብ ተችሏል

You are currently viewing በኮሜሳ የመሪዎች ጉባኤ ላይ ኢትዮጵያ የዲጂታል መሠረተ ልማት ለሀገር በቀል ኢኮኖሚ ዕድገት ቁልፍ ጉዳይ አድርጋ እየሰራች መሆኑን ማስገንዘብ ተችሏል
  • Post category:አፍሪካ

AMN መስከረም 30/2018

በምስራቅና ደቡብ አፍሪካ ሀገራት የጋራ ገበያ(ኮሜሳ) የመሪዎች ጉባኤ ላይ ኢትዮጵያ የዲጂታል መሠረተ ልማት ለሀገር በቀል ኢኮኖሚ ዕድገት ቁልፍ ጉዳይ አድርጋ እየሰራች መሆኑን ማስገንዘብ እንደቻለች የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊ ቢልለኔ ስዩም ገለጹ።

24ኛው የምስራቅና ደቡብ አፍሪካ ሀገራት የጋራ ገበያ(ኮሜሳ) የመሪዎች ጉባኤ ትናንት በኬንያ ናይሮቢ ተካሂዷል። በጉባኤው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)ን ጨምሮ ከኮሜሳ አባል ሀገራት የተውጣጡ የሀገራት መሪዎች ተሳትፈዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በጉባኤው ባደረጉት ንግግር ዲጂታላይዜሽን የኢትዮጵያ የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ አጀንዳ ወሳኝ ምሰሶ መሆኑን አንስተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደ የኮደርስ ስልጠና ኢኒሼቲቭ ባሉ ጠንካራ የዲጂታል መሠረተ ልማት በመገንባትና ሰፊ ክህሎት ከማፍራት አኳያ ኢትዮጵያ አመርቂ ውጤቶችን በማስመዝገብ ላይ እንደምትገኝ መጥቅሳቸውን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊ ቢልለኔ ስዩም ተናግረዋል፡፡

እነዚህ ዘርፈ ብዙ ጥረቶች የኢትዮጵያን ዕድገትና ለውጥ ለመምራት ብሎም ጠንካራ ዲጂታል መሠረተ ልማት ለመፍጠር ያላትን ቁርጠኝነት የሚያሳዩ መሆናቸውንም ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያ የጀመረችውን የብሔራዊ መታወቂያ ሥርዓትና የመንግሥት አገልግሎቶችን አውቶሜት የማድረግ ተግባራት ለዲጂታል ዘርፉ እድገት እንደ ቁልፍ ምሳሌዎች የሚወሰዱ መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡

እንደ ኮደርስ ስልጠና ኢኒሼቲቭ ያሉ መርሐ ግብሮች ወጣቶች የዲጂታል ክህሎትን በመታጠቅ እና በዘርፉ ትርጉም ያለው ለውጥ እንዲያመጡ የሚያስችሉ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው የሀገር ውስጥ የዲጂታላይዜሽን ጥረቶች ከፍተኛ ውጤት እንዲያስገኙ ከቀጣናዊ ግቦች ጋር መጣጣም እንደሚገባም መናገራቸውን ኃላፊዋ ገልጸዋል፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊ ቢልለኔ ስዩም አክለውም፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአፍሪካ ወጣቶች ለአህጉሪቱ ልማትና ዕድገት ወሳኝ ሃብት መሆናቸውን ማንሳታቸውን ጠቅሰዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአፍሪካ ሀገራት የአህጉሪቱን የጎለበተ የወጣቶች ተሰጥኦ እና አቅም መጠቀም እንደሚገባቸውም አስገንዝበዋል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review