ኢትዮጵያን ከተረጂነት የማላቀቅ ጥረት አብነቶች

You are currently viewing ኢትዮጵያን ከተረጂነት የማላቀቅ ጥረት አብነቶች

ከተረጂነት ለመውጣት ምርትን በብዛት፣ አይነትና ጥራት ማሳደግ ላይ እንደሚተኮር ተገልጿል

የህዝብ ተወካዮች እና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች የጋራ የመክፈቻ ስነ ሰርዓት በየዓመቱ በመስከረም የመጨረሻው ሳምንት እንደሚካሄድ ይታወቃል። በዚህ ሀገራዊ መድረክ የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ተገኝተው አጠቃላይ ዓመታዊ አፈፃፀምና የመጭው በጀት ዓመት ዋና ዋና ተግባራትና የቀጣይ ጊዜያት የትኩረት አቅጣጫዎች ላይ ገለፃ ያደርጋሉ።

የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት አምባሳደር ታዬ አጽቀስላሴ ባሳለፍነው ሳምንትም በምክር ቤቶቹ 5ኛ ዓመት 1ኛ መደበኛ ስብሰባ መክፈቻ ላይ ተገኝተው በሀገራዊ፣ ቀጣናዊ እና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ላይ ማብራሪያ መስጠታቸው ይታወሳል።

የመጭው በጀት ዓመት ዋና ዋና ተግባራትና የትኩረት አቅጣጫዎችን ሲያብራሩ፣ ከተረጂነት ለመላቀቅና ለኑሮ ተስማሚ የሆነች ሀገርን ለመገንባት ሰፊ ስራዎች ይሰራሉ ብለዋል። ለዚህም የግሉን ዘርፍ ምርታማነት ማሳደግ፣ የስራ ዕድል መፍጠር፣ የኢንዱስትሪ ዘርፍ ማነቆዎችን መቅረፍ፣ ምርትን በብዛት፣ አይነትና ጥራት ማሳደግ ላይ ይተኮራል ሲሉም ተደምጠዋል።

ፕሬዝዳንቱ ከተረጂነት ለመላቀቅ ያግዛሉ ያሏቸው ነጥቦች ምን ያህል አቅም ይሆናሉ? ስንል የጠየቅናቸው የምጣኔያዊ ሀብት ተንታኝ አቶ ኪሩቤል ሰለሞን፣ ነጥቦቹ በቂና ዘላቂ ትኩረት ከተደረገባቸው ለውጥ አምጪ ይሆናሉ፤ ሀገሪቷንም ከተረጂነት አውጥተው ወደተሻለ የእድገት ደረጃ ለማሸጋገር ሁነኛ መደላድል ይፈጥራሉ በማለት ተከታዩን ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

አቶ ኪሮቤል በሰጡን ሙያዊ ማብራሪያ፣ የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀስላሴ እንደሀገር ከተረጂነት ለመላቀቅ ያግዛሉ ብለው ያስቀመጧቸው አቅጣጫዎች ተገቢነት እንዳላቸው ጠቁመው፣ በእነዚህ ጉዳዮች ዙሪያ ተገቢው ትኩረት ተሰጥቶ ከተሰራ ከተረጂነት ለመላቀቅ ሁነኛው ስልት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

ከቀደሙት መንግስታት ጀምሮ ከድህነት ለመውጣት በርካታ ጥረቶች ተደርገዋል ያሉት አቶ ኪሩብል፣ ኢትዮጵያ ደሃ ሀገር እንደመሆኗ ከተረጂነት ለመላቀቅ ሀገር በቀል ሀብትና እውቀት ላይ አብዝቶ መስራት ይመከራልም ብለዋል፡፡ ሩቅ ምስራቅ ያሉ ሀገራት በተለይ ቻይና እና ህንድ ይህን አይነት አካሄድ ተከትለው ተጨባጭ እድገት አምጥተዋልና ኢትዮጵያም በዚያ ረገድ ብትሰራ ይበጃታል ሲሉም መክረዋል፡፡

ኢትዮጵያ ሰፊ የሚታረስ መሬት አላት ያሉት አቶ ኪሩቤል፣ አብዛኛው ዜጋ ወጣትና አምራች ኃይል በመሆኑ የኢትዮጵያን እድገት አስተማማኝ ያደርገዋል፡፡ አሁን ላይ ደግሞ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ተጠናቅቆ ኃይል ማመንጫት በመጀመሩ ቀላል የማይባል እድልና አቅም ይፈጥራል፡፡ አጋጣሚውን በመጠቀም የግብርና እና የኢንዱስትሪ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ፣ ሰፊ የስራ ዕድል በመፍጠር ከተረጂነት መላቀቅ ይቻላል ብለዋል፡፡

እንደ ፕሬዝዳንት ታዬ፣ መንግስት ለዓመታት ሲያጠናና ሲዘጋጅበት ቆይቶ ተግባራዊ ባደረገው የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ እንዲሁም ቀደም ሲል በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ማዕቀፍ ተይዘው በተከታታይ ዓመታት ተግባራዊ ሲደረጉ በቆዩ ፕሮግራሞች የሀገሪቱ ኢኮኖሚ በማንሰራራት ላይ ይገኛል፡፡

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ለዘመናት በመዋቅራዊ ተግዳሮቶች ተፅዕኖ ስር ወድቆ በከፍተኛ የእዳ ጫና ውስጥ ይገኝ እንደነበር ያስታወሱት ፕሬዝዳንቱ፣ ከለውጡ በፊት ይመዘገብ የነበረው እድገትም በዘላቂ የፋይናንስ መሰረት ላይ ያልተዋቀረ ሀገርን ለከፍተኛ እዳ የዳረገና የማክሮ ኢኮኖሚ መዛባቶችን የፈጠረ እንደነበር ጠቁመዋል፡፡

መንግስት እነዚህን የኢኮኖሚ መዛባቶች የሚያርሙና ወደ ብልፅግና ጎዳና የሚያደርሱ መጠነ ሰፊ የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች ተግባራዊ አድርጓል፡፡ በዚህም የመንግስትን ገቢ፣ የውጭ ንግድ ወይም ኤክስፖርት እንዲሁም የውጭ ምንዛሪ ክምችት ለማሳደግ ከመቻሉም በላይ የልማት አቅጣጫው ትኩረትም ውስን ከሆኑ ዘርፎች ወደ ባለብዙ ዘርፍ የኢኮኖሚ መሰረቶች በመቀየር ላይ ይገኛል ነው ያሉት፡፡

ኢኮኖሚውን ከእዳ ጥገኝነት በማላቀቅ ወደ ኢኮኖሚያዊ ሉዓላዊነት ማሸጋገር የሚያስችል ተግባር ተከናውኗል ብለው፣ የኢኮኖሚ አቅሞችን ማወቅ፣ በችግር ውስጥ እድልን ማየት፣ በፈጠራና በፍጥነት፣ በትብብርና የተለያዩ አቅሞችን በማሰባሰብ እንዲሁም ዘላቂ ግቦችን በማሳካት ላይ ያተኮሩ ናቸውም ብለዋል፡፡

እነዚህ መሰረቶች አጠቃላይ ሀገራዊ እድገትን ለማፋጠን አስችለዋል፤ በዚህም ከዕዳ ጫና በመላቀቅ በራስ አቅም ችግሮችን በመፍታት ከአግላይ የኢኮኖሚ እስራት ወደ አሳታፊና ምቹ የኢኮኖሚ ምህዳር በመሸጋገር፣ ከዝናብ ጥገኝነት ወደ ራስ ቻይ አምራችነት በመብቃት፣ የማዕድን ጥሪታችንን ወደ ወሳኝ የሀብት ምንጭነት በመቀየር የቱሪዝም ሀብታችንን ከመዳህ ጉዞ ወደ ጉልህ የእድገት አንቀሳቃሽነት በማሳደግ የህዝባችንን የአኗኗር ዘይቤ ለመለወጥና ዘላቂ ተጠቃሚነቱን ለማረጋገጥ ከፍተኛ ጥረት ተደርጓል ሲሉም አክለዋል፡፡ ይህም የተረጂነት ሁኔታን የሚቀንስ መሠረት እንደሆነ ገልፀዋል፡፡

በቀጣይም መንግስት መሰብሰብ ያለበትን ገቢ መሰብሰብ፣ የኢንቨስትመንት ማበረታቻዎችን በአግባቡ ጥቅም ላይ መዋላቸውን ክትትል ማድረግ፣ ተወዳዳሪ የሆነ የኢንዱስትሪ ሴክተር እንዲኖረን መስራት ያስፈልጋል ብለዋል ፕሬዝዳንቱ።

ፕሬዝዳንት ታዬ፣ ኢትዮጵያ በብዛት በእህል እንዲሁም በሌሎች መስኮችም ተረጂ ሀገር መሆኗን ጠቅሰው፣ ይህን ችግር ለመቅረፍ ዋነኛ መፍትሔው ምርትና ማርታማነትን ማሳደግ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡

የምጣኔያዊ ሀብት ተንታኙ አቶ ኪሩቤል በበኩላቸው፣ የሚታረስ መሬት ማስፋትና ማዘመን፣ የሚመጡትን ኢንቨስትመንቶች ደግሞ በጥንቃቄ መርጦ ስራ ላይ ማዋል የሀገሪቱን የኢንዱስትሪ ምርት በከፍተኛ ሁኔታ ይጨምራል ባይ ናቸው፡፡

ምርታማነት ይደግ የተባለው ለግብርና ከሆነ የሚያስፈልገን ማዳበሪያ ነው፤ ለኢንዱስትሪና ኮንስትራክሽን ሴክተሩ ከሆነ ደግሞ ሰፊ የሆነ የሲሚንቶና የብረት ማቅለጫዎች እንዲሁም ለበርካታ ወገኖች የስራ እድል መፍጠር ከሆነ በጨርቃ ጨርቅ፣ ብረታ ብረትና ሌሎች ዘርፎች ትልልቅ ኢንዱስትሪዎችን መስራት አስፈላጊ እንደሆነም ይመክራሉ፡፡

ከተረጂነት ለመላቀቅ እንደሚተኮርባቸው ከተጠቀሱት ጉዳዮች በተጨማሪ ለግሉ ዘርፍ የሚሰጠውን ማበረታቻ መጨመርና ምቹ ሁኔታ መፍጠር ከተቻለ የታሰበውን ያህል ማሳካት እንደሚቻል ጠቁመው፣ ከምንም በላይ ግን ዘርፎችን መለየት፣ የት እንድረስ? የሚለውን ግብ ማስቀመጥ፣ ለቦታው የሚመጥኑ ሰዎችን ማሳተፍ ተገቢ እንደሆነ አቶ ኪሩቤል ተናግረዋል፡፡

ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በተጨማሪም የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ኢትዮ ቴሌኮምን የመሳሰሉ ተቋማት የተመሩበት አመራር ቀልጣፋ፣ ዘመናዊና በየጊዜው ለለውጥ ራሳቸውን የሚያዘጋጁበት መንገድ በዙ ተሞክሮ የሚወሰድበት ነው። ይህን ጥንካሬ በሌሎችም ሴክተሮች መድገም ይቻላል ያሉት አቶ ኪሩቤል፣ እነዚህ ነገሮች ተግባራዊ ከተደረጉ ፕሬዝዳንቱ ባስቀመጡት አቅጣጫ መሠረት ምርታማነትን ማሳደግ እና ከተረጅነት መውጣት ከመቻልም ባሻገር ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ እድገት ማምጣት ይቻላል ብለዋል፡፡

ይህን ለማሳካትም መንግስት በተለያየ መንገድ ለህዝቡ ማስረፅ፣ ህዝቡም በስራ መለወጥ እንደሚቻል በማመን በተሰማራበት መስክ ሁሉ ጠንክሮ መስራት እና ከምንም በላይ ስራን ማስቀደም አለበት ሲሉም መክረዋል፡፡

በሸዋርካብሽ ቦጋለ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review