በለይላ መሀመድ
ልጆች እንዴት ናችሁ? ዛሬ የምናስተዋውቃችሁ በእረፍት ቀናችሁ አእምሯችሁን እና አካላችሁን ዘና የምታደርጉበት የህፃናትና ወጣቶች ቴአትርና ሲኒማ ኮምፕሌክስን ነው። የህፃናትና ወጣቶች ቴአትርና ሲኒማ ኮምፕሌክስ የተገነባው በከተማ አስተዳደሩ ሲሆን ዘመናዊ እና ለእናንተ ለልጆች የሚመጥን ተደርጎ ነው የተገነባው፡፡
አቶ ሀብታሙ ተክሉ በኮምፕሌክሱ በኃላፊነት እንዲሠሩ የተመደቡ ናቸው፡፡ ስለአዲሱ የቴአትርና ሲኒማ ኮምፕሌክስ ምን እንደሚመስል እና በውስጡ ምን ምን እንደያዘ ይገልፁላችኋል፡፡ ልጆች በአካል ተገኝታችሁ ጥበባዊ መሰናዶዎችን እስክትታደሙበት ወይም እስክትጎበኙት ድረስ የእሳቸው ገለፃ ለግንዛቤ ይጠቅማችኋልና ተከታተሏቸው፡፡
ሀብታሙ ተክሉ እባላለሁ በአዲስ አበባ ከተማ የቴአትር ቤቶች አስተዳደር ድርጅት የህጻናትና ወጣቶች ቴአትር ዳይሬክተር ነኝ፡፡ በቅርቡ የተመረቀውን አዲሱ የህፃናትና ወጣቶች ቴአትርና ሲኒማ ኮምፕሌክስ በጥቂቱ ላስተዋውቃችሁ፡፡ ይህ ኮምፕሌክስ ዓለም አቀፍ ደረጃውን ጠብቆ የተገነባ ነው፡፡
ሕንፃው ግዙፍ እና ዘመናዊ ሲሆን በውስጡ 1 ሺህ 200 ሰዎችን በአንድ ጊዜ መያዝ የሚችል ትልቅ የቴአትር አዳራሽ፣ ደረጃቸውን የጠበቁ ሁለት ሲኒማ ቤቶች የሚገኙ ሲሆን እነዚህ ሲኒማ ቤቶች እያንዳንዳቸው 168 እና 158 ሰዎችን በአንድ ጊዜ ማስተናገድ ይችላሉ። ትልቁ የቴአትር ቤትና ሁለቱ የሲኒማ ቤቶች እንደ ተመልካቾቹ ብዛት ቴአትር እና ፊልም ማሳየት ያስችላሉ፡፡
ይህ ለአዲስ አበባ ህፃናትና ወጣቶች ብቻ ሳይሆን ወደ ከተማዋ ከተለያየ አካባቢ ጎራ ለሚሉ ህፃናትና ወጣቶች ትልቅ ጠቀሜታ አለው። እንዲህ ዓይነት ሥራን ከተማ አስተዳደሩ በማከናወኑ እኔ ደስ ብሎኛል፡፡ እናንተም እንኳን ደስ አላችሁ ልጆች፡፡
ልጆችዬ አዲሱ የቴአትርና ሲኒማ ኮምፕሌክስ ከዚህ በፊት ከነበሩት የቴአትር እና ሲኒማ ቤቶች በብዙ ነገሩ ይለያል፡፡ መድረኩ ትልቅ ነው። አሠራሩ ልዩ ነው፡፡ ደግሞም በጣም ዘመናዊ ነው። ከዚህ በፊት ወደ ቴአትር ወይም ሲኒማ ቤቶች ሄዳችሁ የምታውቁ ከሆነ፤ አዲሱን ስትመለከቱት ልዩነቱን ትረዳላችሁ፡፡ የአዲሱ የቴአትርና ሲኒማ ኮምፕሌክስ መድረክ በኮምፒውተር አማካኝነት በራሱ እንዲንቀሳቀስ ተደርጎ ነው የተሠራው፡፡
የሚንቀሳቀሰው ዋና መድረክ ሦስት ክፍሎች አሉት፡፡ ይህ በተለይም የልጆች ቴአትር በባህሪው የተለየ በመሆኑ ባህሪውን ታሳቢ ያደረገና በታሰበው ልክ ለማዝናናት የሚያገለግል ነው።
የህጻናት ቴአትር እንደ አዋቂዎች መድረክ ላይ ብቻ የሚሰራ ሳይሆን መውጣት፣ መውረድ፣ መነሳትና መሽከርከር ያለበት በመሆኑ ነው። እንዲህ ዓይነት ተንቀሳቃሽ መድረክ በእንግሊዘኛ ቋንቋ ሀይድሮሊክ ስቴጅ (Hydrolic stage) ይባላል፡፡ መድረኩ እንደአስፈላጊነቱ ወደላይና ወደታች የሚንቀሳቀስ ነው፡፡ ተዋናዮቹን እንደአስፈላጊነቱ ወደታች ወደ መሬት ይዞ ይሄዳል፡፡ መልበሻ ክፍል ይወስዳል። ደርሰው ልብስ ቀይረው ሲመለሱ ይቀበላል፡፡ መድረኩ ላይ ያልታየን ነገር በተንቀሳቃሹ መድረክ አማካኝነት ድንገት እንዲወጡ ማድረግ ያስችላል፡፡ በተጨማሪም፤ የማሳያ ስክሪኑ የሚቀያየረውን ምስልና ብርሃንም በኮምፒውተር አማካኝነት ዲጂታላይዝድ በሆነ መንገድ የሚሠራ ነው፡፡
ሌላው መድረክ ላይ የሚተውን ሰው ድንገት በአእምሮው የያዘው ቢጠፋበት ወይም ንግግር እያደረገ በመሀል ቢጠፋው የሚያስታውሰው ጠቋሚ(Tele prompt) አለው፡፡ ይህም በኮምፒውተር አማካኝነት የሚሠራ ቴክኖሎጂ ነው፡፡ ያለማንም ሠው ድጋፍ ለተናጋሪው ግልጽ መረጃ የሚሰጥ ሰፊ ስክሪን ተገጥሞለታል። ለተዋናይ አማራጭ የሚሰጥ በመሆኑ ጠቀሜታው ከፍተኛ ነው፡፡ ከመድረኩ ግራና ቀኝ በኩልም የማሳያ ስክሪኖች አሉት፡፡ እንዲህ አይነት መድረክ እንደ ሀገር የመጀመሪያና አዲስ ነው፡፡
ለኮንፈረንስና ሲምፖዚየም የሚያገለግሉ ሶስት ትላልቅ አዳራሾችም በህንጻው ውስጥ ይገኛሉ፡፡ 11ኛ ፎቅ ቴራስ ላይ ደግሞ ሶስት ደረጃቸውን የጠበቁ ካፌና ሬስቶራንቶች አሉ፡፡ ከቴአትር ትወናና ሙዚቃ ጋር በተያያዘ ልምምድ የሚደረግባቸው ወርክሾፖች፣ መልበሻ፣ መታጠቢያ ክፍሎችም በሕንጻው አሉ፡፡ የህጻናት መጫወቻዎች በህንጻው የመሬት ክፍል ተሰርቷል፡፡ የህጻናት ቤተመጻህፍትም አለው፡፡ 300 መኪናዎችን ማቆም የሚችል የመኪና ማቆሚያ በመሬት ውስጥ ተዘጋጅቷል፡፡
አዲሱ የቴአትርና ሲኒማ ኮምፕሌክስ ህጻናት ያላችሁን የፈጠራ ክህሎት ያሳድግላችኋል፡፡