ቅርሶች በታሪክ ተከስቶ የነበረ የህዝቦች ሥልጣኔን ብሎም የዕድገት ደረጃ የሚጠቁሙ ቋሚ ምስክሮች ናቸው፡፡ ባህል ደግሞ የህዝቦችን ቋንቋ፣ አለባበስ፣ የሥራ መገልገያ መሣሪያዎች፣ ወጎች፣ ልማዶች እና ሌሎች ሥርዓቶችን ያካትታል። በተለይ ደግሞ በሀገራችን በርካታ የሚዳሰሱ ብሎም የማይዳሰሱ ቅርሶች በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) አማካኝነት እውቅና አግኝተው የተመዘገቡ ናቸው። ከማይዳሰሱ ቅርሶቻችን መካከል እንደ መስቀል፣ የገዳ ስርዓት፣ ጥምቀት፣ ፊቼ ጨምባላላ፣ ሸዋል ኢድ እንዲሁም ሄር-ኢሴ ተጠቃሾች ናቸው፡፡ የሚዳሰሱ ቅርሶቻችንን በተለመከተ እንዲሁ የላል ይበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት፣ የሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ፣ የፋሲል ግንብ ( ጎንደር)፣ የአክሱም ሐውልት፣ የታችኛው አዋሽ ሸለቆ፣ የጢያ ትክል ድንጋይ፣ የታችኛው ኦሞ ሸለቆ፣ ሐረር ጀጎል ጥንታዊ ከተማ፣ የኮንሶ ባህላዊ መልክዓ-ምድር፣ የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ፣ የጌዲኦ ባህላዊ መልክዓ ምድር፣ መልካ ቁንጡሬ ባልጩት አርኪዮሎጂና ፓሎአንትሮፖሎጂ ተጠቃሾች ናቸው፡፡
በወርሃ መስከረም የቱሪዝም ቀን ይከበራል፡፡ ይህንንም ተከትሎ በተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች የሚከበሩ የዘመን መለወጫ በዓላት፣ መስቀል፣ ኢሬቻ እና መሰል በዓላት ላይ የሚታደሙ የሀገር ውስጥና የውጭ ጎብኚዎች ቁጥር ከሌላው ጊዜ ይጨምራል፡፡ ከዚህ ቀደም ላለፉት ውስን ዓመታት ሀገራችን በሰው ሰራሽና በተፈጥሮ አደጋ ምክንያት ጎብኚዎች በሚፈለገው ልክ ሊጎበኟት አልቻሉም ነበር፡፡ አሁን ግን በርካታ አስቻይ ሁኔታዎችን በመንግስት እንዲሁም ቅርሶቹ በሚጎበኙባቸው አካባቢዎች ላይ ተገቢውን ስራ ለመሰራት በመቻሉ የሀገር ውስጥ ብሎም የውጭ ጎብኚዎችን ቀልብ ለመሳብ ተችሏል፡፡
አያሌው ሲሳይ (ዶ/ር) ከፍተኛ የቱሪዝም ተመራማሪ እና መምህር ናቸው፡፡ እሳቸው እንደሚገልፁት፤ የኢትዮጵያውያን የብዝሃ ማንነት መገለጫዎቿ በርካታ ናቸው። የሰዎች የሰውነት እንቅስቃሴዎች (ጭፈራዎች)፣ ሙዚቃ፣ ሥነ-ቃል እና የመሳሰሉትን ተከትሎ የሚካሄዱ ሃይማኖታዊ ብሎም ባህላዊ ክንውኖች በማይዳሰስ ቅርስነት የሚመዘገቡ ናቸው። በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች የሚገኙ ጥንታዊ ኃይማኖታዊ እና ታሪካዊ ቦታዎች እና የኪነ ሕንጻ ሀብቶቻችን የብዝኃነታችን ውጤቶች ናቸው፡፡ ኪነ ሕንጻዎቻችን ለብዝኃነታችን ውበት እና አቅም ማሳያዎቻችን ናቸው። በተለያዩ ዘመናት፣ ለተለያዩ ዓላማዎች መሠራታቸዉ የሐሳብ እና የዕውቀት ብዝኃነታችንን ምንም ቴክኖሎጂ ባልነበረበት ወቅት ዘመን ተሻጋሪ ተደርገው መሠራታቸው አሁን ላለንበት ጥሩ አቅም ፈጥረውልናል፡፡

ሀገራችንም እነዚህን ቅርሶች አስፈላጊውን እንክብካቤ በማድረግ ለጎብኚዎች ክፍት ከማድረግ ባሻገር እንደ አንድ የገቢ ምንጭነት ምን ያህል ተጠቅማበታለች የሚለውን ጉዳይ በተመለከተ አያሌው (ዶ/ር ) አስረድተዋል፡፡ “የቱንም ያክል የሚጎበኙ ቅርሶች ቢኖሩን እንኳን እንዴት የገቢ ምንጭ ሆነው የሀገር ኢኮኖሚን ለመደገፍ አስችሏል” በሚል እቅድ አውጥቶ መስራት ያስፈልጋል፡፡ የሀገር ውስጥ ብሎም የውጭ ጎብኚዎችን ለማስተናገድ ልንከተላቸው ከሚገቡ ስልቶች መካከል አንዱ የሆነው የጉብኝት ፓኬጅ ማዘጋጀት ነው፡፡ አንድ አስጎብኚ ድርጅትም በእውቀት የታገዘ ብቁ እና የሀገርን ባህልና ወግ ጠንቅቆ በአግባቡ ሊያስረዳ የሚችል አስጎብኚን መቅጠር ይጠበቅበታል፡፡ የአስጎብኚነት ስራ የቋንቋ ችሎታ ስላለ ብቻ የሚከወን ተግባር መሆን የለበትም፡፡ ጥሩ እውቅናን ካተረፉ የመንግስት ቴክኒክና ሙያ እንዲሁም ጥሩ የማስተማር ብቃት ካለው የግል ትምህርት ቤት ተመራቂዎችን መቅጠር ያስፈልጋል የሚል እምነት አላቸው፡፡
የጎብኚዎችን ቁጥር ለማሳደግ የተጎዱ ቅርሶችን ቀድሞ የነበራቸውን ይዞታ ሳይለቁ ማደስ እና እንደ አዲስ ማስዋብ ያስፈልጋል። ለዚህ ደግሞ የኢትዮጵያ ወዳጅ ሀገራት ለሚያደርጓቸው ድጋፎች አምባሳደሮቻችን መልካም በሆነ የገፅታ ግንባታ ላይ መስራት ይጠበቅባቸዋልም ብለዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በተለይ ከአዲስ አበባ ውጪላሉ አካባቢዎች የውሃ እና የመብራት አቅርቦቶችን ማስተካከል፣ ምቹ የመኪና መንገድ እንዲኖር ማድረግ እንዲሁም ሆቴሎችን በተመጣጣኝና በሀገሬው ዋጋ ማስተናገድ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡
አያሌው (ዶ/ር) አያይዘውም፤ የውጭ ሀገር ብሎም የውስጥ ጎብኚዎች የቆይታ ጊዜውን ለማራዘም የሚችሉባቸውን የተለያዩ የጉዞ ፕሮግራሞች ማውጣት ያስፈልጋል፡፡ ጎብኚው እየተዝናና ጥሩ ጊዜ እያሳለፈ “መች ይሆን በድጋሜ የምመጣው?” የሚለውን በጎ ሃሳብ በውስጣቸው እንዲጭሩ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ከዚህ ቀደም በነበረው አሰራር ጎብኚዎች በሚኖራቸው ቆይታ ምቾት ሳይሰማቸው ይቆዩና በቶሎ ለመመለስ ይሻሉ፡፡ አሁን ግን መንግስት የተለያዩ ዘመናዊና የጎብኚዎችን ምቾት ባስጠበቀ አግባብ ተግባራዊ ያደረጋቸው የቱሪዝም መዳረሻ ስፍራዎች አማካኝነት አጓጊ ብሎም ትዝታን የሚያጭር ስፍራዎችን ለማዘጋጀት መቻሉ ትልቅ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ አለውም ብለዋል፡፡
በተለይ አንድ ጎብኚ የቆይታውን ጊዜ ለማራዘም የቻለ እንደሆነ ተጨማሪ ወጪ የሚያደርጋቸው ጉዳዮች ይኖሩታል፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ሀገራት ደግሞ ትልቅ ፋይዳ እንደሚኖረው አያሌው (ዶ/ር) ተናግረዋል። ቅርሶቻችን የሀገራችን ትልቅ ሃብቶች ናቸው፡፡ ጥበቃና ልዩ እንክብካቤን ይሻሉ፡፡ እንደ ሀገር ያስመዘገብናቸው ቁጥራቸው ወደ 18 የሚጠጉ ቅርሶች በዓለም አቀፍ ራሳችንን በደንብ እንድናስታውሰው ያግዘናል። በተለይም ለሀገር ገፅታ ግንባታ እጅግ ትልቅ አበርክቶ አለው፡፡

“’ለካ ኢትዮጵያ እንዲህ ያለች ሀገር ናት’ በሚል ተደጋጋሚ ቱሪስቶች ወደ ሀገራችን መምጣት መቻላቸው የትራንስፖርት ዘርፍ፣ ሆቴሎች፣ አስጎብኚ ድርጅቶች እንዲሁም የመዲናዋ ብሎም የሀገሪቱ ነዋሪዎች ይነቃቃሉ፡፡ ቅርሶቻችንን በሚገባ ባስተዋወቅንና አስፈላጊውን ጉዳይ ከስር ከስር ማሟላት ከቻልን የኢኮኖሚው ሴክተር በሀገር አጠቃላይ ገቢ ላይ ትልቁን አሻራ እንዲያኖር እድል ፈንታ ይፈጥራል” ሲሉ ሀሳባቸውን አጋርተውናል፡፡
“አዲስ አበባ ላይ የሚገኙ ቅርሶችን በማስጎብኘት መዲናዋ የራሷን ገቢ ለማሳደግ ምን አይነት አስቻይ ሁኔታ አለ?” ስንል ላነሳንላቸው ጥያቄ አያሌው (ዶ/ር) በምላሻቸው፤ “በሚያስደንቅ ሁኔታ አዲስ አበባ የዘመናት አቧራዋን አራግፋ ዳግም ታድሳ ለነዋሪዎቿ ብሎም በሩቅ ለሚያውቃት አዲስ ሙሽራ ሆናለች። በእቅድና ከፍተኛ ወጪ በማውጣት ጭምር ጎብኚዎች ጥሩ ጊዜ ለማሳለፍ ከሀገር ሀገር ይጓዛሉ። የመጓዛቸው ሚስጥርም ታሪካዊ እና የተፈጥሮ ጥበብን ለማድነቅ መሆኑ ነው። ቱሪዝም የዓለም ህዝቦችን እርስ በእርስ እንዲተዋወቁ ባህል እና ወግ ልምዳቸውን እንዲጋሩ መልካም እድልን ይፈጥራል” ብለዋል፡፡
እንደ አያሌው (ዶ/ር) ገለፃ፤ አዲስ አበባ ላይ የሚገኙ ቅርሶች ሰው ሰራሽ ብሎም በተፈጥሮ የታደልናቸው ናቸው። እንደሚታወቀው ከጥቂት ዓመታት በፊት ትላልቅ የአይን ማረፊያ ፓርኮች እና ሙዝየሞች ለአይን በሚማርክ አግባብ ለጎብኚዎች ክፍት ተደርገዋል። ዘመኑን የዋጀ የሰለጠነው ዓለም የደረሰበትን የአሰራር ስርዓት በመከተልም በርካታ ጎብኚዎችን ተደራሽ ያደረገ ስራ ተሰርቷል፡፡ ለበርካታ ዓመታት የአፍሪካ ጉባኤን ስታስተናግድ የነበረችው አዲስ አበባ እንግዶቿን ለመቀበል ብሎም የቆይታ ጊዜያቸውን ለማራዘም አስቻይ የሚባሉ ሁኔታዎች በስፋት አልነበሩም። መዲናዋ በእጇ ላይ ያሉ ሀብቶቿን በአግባቡ በማልማት፣ በማስዋብና በማደስ የተደበቀውን ሃብት አንድ ሁለት ብሎ እንዲወጣ እያደረገች ትገኛለች። አፈር ለብሰው የነበሩ ታሪካዊ ቅርሶች ደረጃቸውን በጠበቀ አግባብ እድሳት በማድረግ ወደ መስህብነታቸው መመለስ ስለመቻላቸው አስረድተዋል፡፡

አዳዲስ የቱሪስት መዳረሻዎች በስፋት መገንባታቸውም የከተማዋን ገፅታ በማሻሻል ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነቷን ከፍ እንደሚያደርገው አያሌው (ዶ/ር) ገልፀዋል፡፡ አያይዘውም፤ የኮንፍረንስ ቱሪዝም መነቃቃት ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ ከተማ የመገንባት እሳቤን ከማራመድ አንፃር ጥሩ እመርታ ላይ ትገኛለች። ዘርፈ ብዙ ግልጋሎቶችን መስጠት በሚያስችል አግባብ የተገነባው አዲስ ዓለም አቀፍ የኤግዚቢሽን እና ኮንቬንሽን ማዕከልም መነቃቃት ለጀመረው የመዲናዋ የኮንፍረንስ ቱሪዝም ዕድገት ሚናው የላቀ እንዲሆን ያደርገዋልም ሲሉ አብራርተዋል፡፡
አያሌው (ዶ/ር) አያይዘውም፤ ቅርሶችን በአግባቡ መያዝ ብሎም ጥበቃ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ በተለይ ረጅም ዓመት ያስቆጠሩትን በማደስ አስፈላጊውን ክትትል ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ለዚህ ደግሞ የሀገር ውስጥ ብሎም የውጭ ባለሃብቶችና ድርጅቶች በእድሳቱ ሂደት እጃቸውን ማስገባት አለባቸው፡፡ በእቅድ የተዘጋጁ የጉብኝት መርኃ ግብሮች ሳቢና አጓጊ በሆነ ጥቅል ፕሮግራም ማሰናዳት ያስፈልጋል። ለዚህ ማስፈፀሚያ ይሆን ዘንድ ደግሞ አስጎብኚ ድርጅቶች ተወዳዳሪ የሆነ ሃሳብ ይዘው መቅረብ ይኖርባቸዋል፡፡ በዘልማዳዊ የሚሰራን ስራ በማስቀረትም በእውቀት የታገዘ አገልግሎት መስጠት ያስፈልጋል። የሚጎበኘው አካል ስለምን ማወቅ ይፈልጋል የሚለውን በማጤን ጥሩ ዝግጅት በማድረግ ማብራራት እንደሚጠበቅባቸው ጠቁመዋል፡፡
መዲናችን አዲስ አበባም ከዚህ ቀደም ከተለመዱ ውስን ጉባኤዎች በእጥፍ የላቁ ዓለም አቀፍ ኩነቶችን በስኬት በማስተናገድ ላይ ትገኛለች፡፡ ለአብነትም በተጠናቀቀው 2017 የበጀት ዓመት 150 ዓለም አቀፍ ኩነቶችን በከፍተኛ ስኬት ያስተናገደች ሲሆን 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ያህል ጎብኚዎችንም አስተናግዳለች። በዚህም 143 ቢሊዮን ብር ያህል ሀብት ወደ ኢኮኖሚያችን ገቢ ሆኗል። ለዚህ ከፍተኛ ውጤት መመዝገብ አዲስ የተገነቡ ፣ የታደሱ ነባር የቱሪዝም መሰረተ ልማቶች፣ የከተማችን ነዋሪዎች የእንግዳ ተቀባይነትና ተባባሪነት ፣ የግሉ ዘርፍ የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት እና የመንግስት የተናበበ ቅንጅት፣ ጉልህ ድርሻ ስለመሆኑ የአዲስ አበባ ቱሪዝም ኮሚሽን በማህበራዊ ገፀ ድሩ ላይ አስፍሯል፡፡
በሄለን ጥላሁን