የመደመር መንግሥት መጽሀፍ ኢትዮጵያውያን ለምን ወደኃላ ቀረን የሚል ቁጭት የወለደውና ወደቀደምት ገናናነቷ ለመመለስ እንዲሁም ከድህነት መውጫ መንገድን አመላካች ነው ሲሉ ምሁራን ተናግረዋል። በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ የትምህርት አመራሮች በመደመር መንግሥት መጽሃፍ ላይ የፓናል ውይይት እያካሄዱ ነው።
በውይይቱ ምሁራን የመጽሀፉ ሀሳብና ጭብጥ ላይ ሙያዊ እይታቸውን አጋርተዋል። በኮተቤ ትምህርት ዩኒቨርሲቲ መምህር የሆኑት ዮሴፍ ቤኩ (ዶ/ር)፣ መጽሀፉ የሀገር መሪው ካሳለፉት የህይወት ውጣ ውረድና የመሪነት ሚና ባካበቱት ልምድ ኢትዮጵያዊያን ለምን ወደ ኃላ ቀረን በሚል ቁጭት መነሻ ያደረገ ነው ብለዋል።
በዚህም መነሻነት ወደ ቀደምት ገናናነቷ ለመመለሰና ከድህነት መውጫ መንገድን አመላካች የሆኑ መፍትሄዎችንም ያስቀምጣል ነው ያሉት ። በተለይ መጽሀፉ ቋንቋና ብሔርን ምክንያት በማድረግ የእርስ በእርስ ክፍፍል የሚፈጥሩ አስተሳሰቦችን በብርቱ የሚተችና አዳዲስ አስተሳሰብን፣ ፍልስፍናንና ርዕዮተ ዓለምን ያካተተ ስለመሆኑም አንስተዋል።
በተለዋዋጭ አለም ውስጥ ኢትዮጵያ ያለችበትንና የደረሰችበትን ደረጃ በመጠየቅ የሀገር አለማደግና ድህነት በጸሀፊው በቁጭት መታየቱንም ተናግረዋል።
እንደ ኢትዮጵያ ማደግ ለሚፈልጉ ሀገራትም አስፈላጊ እሳቤን ያካተተ ስለመሆኑ ነው ምሁሩ ያመላከቱት። የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፍልስፍና መምህርና ተመራማሪው ዳኛቸው አሰፋ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ መጽሀፉ የማህበራዊ ፖለቲካ ስብራትን ማሳየቱን ዳሰዋል ።
ምክኒያታዊነትን አብዝቶ የሚያወድሰው መጽሀፉ፣ ችግር ለመፍታት ከብዙ ወገን መዘጋጀት ያስፈልጋል ብሎ እንደሚያምንም ተናግረዋል። ጊዜን መርሁ ያደረገው መጽሀፉ፣ የወደፊቱን ይተልማል፣ ያለውን ይጠብቃል ነው ያሉት ምሁሩ።
በመደመር መንግሥት መጽሀፍ ጭብጦች ላይ ባተኮረው የውይይት መርሀ ግብር መምህራኑ የተለያዩ ሀሳቦችን እያነሱ ይገኛሉ።
በ -አንዋር አህመድ