ሰንደቅ አላማ እና ኪነ-ጥበብ

You are currently viewing ሰንደቅ አላማ እና ኪነ-ጥበብ

AMN – ጥቅምት 2/2018 ዓ.ም

ሰንደቅ አላማ የሚለው መጠሪያ “ሰንደቅ” እና ”አላማ” ከሚሉ ከሁለት ቃላት የተመሰረተ ሲሆን፣ የቃላቱ የተናጥል ትርጉም፡- ሰንደቅ፡- ማለት ምርኩዝ፣ ምሰሶ፣ በትር ማለት ሲሆን ዓላማ ማለት ደግሞ ምልክት፣ አቋም፣ ስብስብ እንዲሁም የነፃነት፣ የሉዓላዊነት ምልክት እንደሆነ ይነገራል፡፡

የሁለቱ ቃላት ጥምረት “ሰንደቅ ዓላማ” የሚለው ቃል በአንድ ላይ የአገር መታወቂያ፣ የሕዝብ አንድነት መጠበቂያ እንዲሁም የክብር መለያ ምልክት የሚለውን ትርጉም የሚሰጥ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ሰንደቅ ዓላማ የአንድ ህዝብንና ሃገር ሉአላዊነት፣ ስልጣንና ነፃነት ምልክት ወይም ተምሳሌት ተደርጎ የሚወሰድ ነው፡፡

ሠንደቅ ዓላማ በእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ልብ የታተመ፣ የሀገራዊ አንድነትና የነፃነት መገለጫ ታላቅ የብሔራዊ ኩራት አርማ ነው፡፡

የብሔራዊ የሠንደቅ ዓላማ ቀን በሠንደቅ ዓላማ አዋጅ ቁጥር 863/2006 (እንደተሻሻለው) አንቀጽ 2 መሰረት በየዓመቱ ጥቅምት ወር በገባ በመጀመሪያው ሳምንት ሰኞ እንደሚከበር ተደንግጓል፡፡

የብሔራዊ የሠንደቅ ዓላማ ቀን በዓል በተለያየ መልኩ በየዓመቱ እየተከበረ አስራ ሰባት ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡

የሠንደቅ ዓላማ ቀን በዓል መከበሩ ሕብረ ብሔራዊ አንድነትን፣ ሉዓላዊነትን፣ በማስጠበቅ የኢትጵያን የከፍታ ብሥራትና ሕዳሴ ለማረጋገጥ ለሀገር ክብርና ጥቅም ሁሉም ዜጋ የሚጠበቅበትን ሀገራዊ ኃላፊነት ለመወጣት በሠንደቅ ዓላማ ፊት ዳግም ቃሉን የሚያድስበት ዕለት ይሆናል፡፡

ታዲያ የሰንደቅ ዓላም ትርጉም እና ክብር ከሚገለፅባቸው ስራዎች መካከል ተጠቃሽ የሆኑት ግጥም እና ዘፈን መሆናቸው ይጠቀሳል ፡፡

በሀገራችን የተለየዩ የኪነ-ጥበብ ባለሞያዎች ስለ ሃገር አንድነት፣ አብሮነት እና ሉዓላዊነት በርካታ የግጥም እና የሙዚቃ ስራዎችን ሰርተዋል፤ ከእነዚህም መካከል አንድ ሁለቱን ማየት ወደድን ፡፡

ህይወቱን ሸለመ

በደሙ ላስዋበሽ

ሰንደቅ አላማችን

ኑሪ እየመሰከርሽ ……

ሰንደቅ ነች ሀይማኖት

አላማ ነች እምነት

አርማ የለሽ ዜጋ

የለውም ነፃነት

አናሳፍርሽም ታሪክ ይወቅሰናል

ዜጎችሽ ዋርድያ

ዘብ ቆመናል

ሰንደቃችን ኑሪ 2*

ኮርተሽ አኩሪ 2*………….

እያለ ድምፃዊው ለሰንደቅ አላማው አንጎራጉሯል ። ጥበበኞች በጥበባቸው፣ በዜማ እና ግጥማቸው ስለ ሰንደቅ አላማ ብዙ ተቀኝተዋል ።

ድምፃዊ ፀጋዬ እሸቱ ሰንደቅ አላማ በሚለው ሙዚቃው ስለ ሰንደቅ አላማ እና ሀገር አስተሳስሮ አዚሟል።

የኔ ልጅ በተሰኘው ስነ-ግጥሙ የሀገር እና የሰንደቅ ዓላማ ትስስር ተቀኝቷል ደራሲና መምህር በድሉ ዋቅጅራ (ዶ/ር)።

ሀገር ማለት የኔ ልጅ

በህሊናሽ የምታኖሪው

ስትወጅ ሰንደቅ ታደርጊው

ቢያስጠላሽ የማትቀይሪው …………… በማለት ሰንደቅ ዓላማ ከፍ አድርገው የሚያውለበልቡት እንደሆነ ይገልፃል።

በዚሁ ስነ-ግጥም ስለ ሀገር ሲያነሳ እንዲህ ይላል ……..

ሀገር ጠላት ሲደፍራት

ጦሩን ሰብቆ እየፎከረ

ኦሮሞው ከትግሬው

አፋሩ ከወላይታ

ከሁሉም የጦቢያ ልጆች

አጥንቱን እያማገረ

ሀገር ይሉት መግባቢያ

ሰንደቅ ይሉት መለያ

ሲያቆይልሽ

በጉራግኛ ማትገልጭው

በጎጥ የማትገድቢው

ስንት ታሪክ አለ መሰልሽ ……….. እያለ ስለሀገር መለያ ሰንደቅ ዓላማ በግጥሙ ለሀገር ያለውን ወገንተኝነትና ፍቅር ገልፆበታል ።

ታዲያ እናንተስ የሰንደቅ ዓላማ ቀንን ስታከብሩ ወደ አዕምሯችሁ የሚመጡ የኪነ-ጥበብ ስራዎች የትኞቹን ያስታውሳሉ?

በ-ሔለን ተስፋዬ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review