የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የስራ ዘመን 1ኛ መደበኛ ጉባኤውን እያካሄደ ይገኛል፡፡
በጉባኤው የምክር ቤት አባላቱ ከመረጣቸው ህዝብ ጋር ባደረጉት የመራጭ ተመራጭ የገፅ ለገፅ ውይይት ምላሽ ያስፈልጋቸዋል ተብለው የተነሱ የህዝብ ጥያቄዎችን ለከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ አዳነች አቤቤ አቅርበዋል፡፡
የተነሱት ጥያቄዎች ፡-
በበዓል ሰሞን እና ምሽትን ተገን በማድረግ የትራንስፖርት ታሪፍ ጭማሪ ነዋሪዎችን ያማረሩ በመሆናቸው ለዚህም በቀጣይ ምን ታስቧል?
ንፁህ የመጠጥ ውሃ ለነዋሪዎች ለማቅረብ ከተማ አስተዳደሩ የያዛቸው እቅዶች ምንድን ናቸው?
በአንድ አንድ የእሁድ ገበያ መደብሮች ከተቀመጠው ዋጋ በላይ ማስከፈል፣ ጥራታቸው ዝቅ ላሉ ምርቶች እኩል ዋጋ መጠየቅ እንደሚስተዋል እና ይህን ችግር ለመቅረፍ በቀጣይ ምን ታስቧል?
በመዲናዋ የኮሪደር ልማት ያልደረሰባቸው አካባቢዎች የኮሪደር ልማትን ለማዳረስ ከተማ አስተዳደሩ ምን አቅዷል?
የጤና ጣብያ እጥረት ያለባቸው አካባቢዎችን ችግር ለመቅረፍ ምን እንደታቀደ ቢገለፅ?

መሰረቱ የማይናወጥ አካታች የወል ትርክት ለመገንባት ብሎም ተራማጅ አስተሳሰብ ማስረጽ፤ የእንችላለን ስነ-ልቦና ብሎም ልመናና ኋላ ቀር አስተሳሰብን በመስበር በኪነ- ጥበብ እያዋዙ ጠንካራ ኢንዱስትሪ ለመገንባትና ዘርፉን ለመደገፍ ከተማ አስተዳደሩ ምን አስቧል?
የኑሮ ሁኔታን በተመለከተ እየተሰራ ያለው ስራ ጎን ለጎን የኑሮ ጫናን ለመቀነስ፣ የነዋሪዎችን እርካታ ለማረጋገጥ የት፣ ምን ተሰርቷል?
በመስከረም ወር የተካሄዱት ታላላቅ በዓላት በስኬት የመጠናቀቃቸውን ያህል በቀጣይም መሰል በዓላት በስኬት እንዲጠናቀቁ ምን ታስቧል? ይሄንንስ ድል እንዴት አገኘነው?
የኮሪደር ልማቱን ህብረተሰቡ በእኔነት እንዲጠብቀው፤ ከተማውን ከተሜ ሆኖ እዲጠብቃት የግንዛቤ ማስጨበጫ ተሰጥቷል ወይ?
ህብረተሰብ ከተማዋን ከተሜ ሆኖ እዲጠብቃት የሕግ ማዕቀፍ አለ? ማዕቀፍ አያስፈልግም ወይ?
ወጣቶች ኮደርስ ስልጠና ወስደው ወደ ስራ አልገቡም፤ ምን ታስቧል?
የፌዴራል መንግስት የሰራተኞች ደሞዝ እንዲስተካከል ወስኗል ከተማ አስተዳደሩ ይህንን ተፈፃሚ ለማድረግ ምን ዝግጅት አድርጓል?
የሚሉ ጥያቄዎች በምክር ቤቱ አባላት የተነሱ ሲሆን ለጥያቆዎቹም በከንቲባ አዳነች አቤቤ ምላሽ ይሰጥባቸዋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
በ- ያለው ጌታነህ