18ኛው ብሔራዊ የሠንደቅ ዓላማ ቀን “ሠንደቅ ዓላማችን ለኢትዮጲያ ታላቅ የከፍታ ዘመን ብሥራት፣ ለብሔራዊ አንድነታችን፣ ለሉዓላዊነታችንና ለኢትዮጲያ ሕዳሴ!” በሚል መሪ ቃል ተከብሯል፡፡
ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀስላሴ ቀኑን አስመልክቶ ባስተላለፉት መልእክት ኢትዮጵያ በቅርብ አመታት ዉስጥ ያጋጠማትን የህልውና ፈተናዎች በህዝቦቿ የአንድነት ክንድ በፅናት ተሻግራ ዛሬ የራሷን ዕድል የመወሰን ብቃት እያስመከረች ትገኛለች ሲሉ ገልጸዋል፡፡
ሰንደቅ ዓላማ የታሪካችን፣ የአንድነታችን እና የሉዓላዊነታችንን ክብር በፅኑ ቀለማት መስካሪ መሆኑን ያነሱት ፕሬዝዳንቱ ሰንደቅ ዓላማችን የታሪከ መዘክር ብቻ ሳይሆን በፈጣን እድገት ላለችው ሀገራችን ድል አብሳሪ እና የጉዞአችን ህያው ምስክር ነውም ብለዋል፡፡
ሀገራችን በቅርብ አመታት ያጋጠማትን የህልውና ፈተናዎች በህዝቦቿ የአንድነት ክንድ በፅናት ተሻግራ ዛሬ የራሷን ዕድል የመወሰን ብቃት እያስመከረች ትገኛለች፤ይህም ሁሉም ዓለም በሚመሰክረው ሀገራዊ ስኬቶች የታጀበ ሲሉ ተናግረዋል፡፡

የኅብረታችን እና የሉዓላዊነታችን ምስክር የሆነው ታላቁ የህዳሴ ግድብ የዚህ አንዱ አብነት ሲሆን አረንጓዴ አሻራ ሥራም ሌላኛው ሀገራዊ ክብር ያስገኘልን ነዉ ሲሉ አመላክተዋል፡፡
የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የተጀመረው ግዙፍ የማዳበሪያ ፋብሪካ እየተገነባ ይገኛል፣ይህም በሚሊዮን የሚቆጠሩ አርሶ አደሮችን ከውጭ የማዳበሪያ ጥገኝነት በማላቀቅ ሀገራዊ ኢኮኖሚያችንን የሚያጠናክር ታላቅ ተግባር ነዉ ሲሉ አብራርተዋል፡፡
የተፈጥሮ ጋዝ ሀብታችንን በመጠቀም ለኢንዱስትሪ ግብዓት እና ለሀይል ማመንጨት ማዋላችን የዕድገትና ብልጽግና ጉዞአችንን ያፋጥናል ነው ያሉት ፕሬዝዳንቱ በንግግራቸው፡፡
ታላላቅ ሥራዎቻች ውጤታማ የሚሆኑት ብሔራዊ አንድነታችን ሲጠናከር እና ሰላማችን አስተማማኝ ሲሆን ነው ያሉት ፕሬዝዳንቱ በልዩነት ውስጥ ያለውን ውበት አክብረን በሀገራዊ ምከክር መድረክ የምንገነባው የጋራ መግባባት ለዘላቂ ሰላም እና ለጠንካራ ዴሞከራሲያዊ ሥርዓት መሠረት እየጣለ ይገኛል ብለዋል፡፡
ሉዓላዊነታችን የሚከበረው በጠንካራ አንድነት እና በበለጸገ ኢኮኖሚ ስንቆም በመሆኑ በቀጣናው ፍትሀዊ የባህር በር የመጠቀም መብታችን በሰላማዊ፣ በዲፕሎማሲያዊ እና በሰጥቶ መቀበል መንገድ ማስከበራችን የሚቀጥል ይሆናል፤ይህ ለኢትዮጵያ ህዳሴ ወሳኝ ጉዳይ ነው ብለዋል ፕሬዝዳንቱ፡፡
በ-በረከት ጌታቸዉ