በመዲናዋ ጥራት ያለው የህክምና አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ እንደሚገኝ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ተናገሩ

You are currently viewing በመዲናዋ ጥራት ያለው የህክምና አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ እንደሚገኝ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ተናገሩ
  • Post category:ጤና

AMN – ጥቅምት 03/2018 ዓ.ም

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በመዲናዋ ጥራት ያለው የህክምና አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ በርካታ ስራዎችን እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የስራ ዘመን 1ኛ መደበኛ ጉባኤውን አካሂዷል።

በጉባኤው ላይ የምክር ቤቱ አባላት በተመረጡበት አካባቢ ከመራጭ ህዝብ ጋር ባደረጉት ውይይት የተነሱ የህዝብ ጥያቄዎችን ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ አቅርበዋል።

ከቀረቡ ጥያቄዎች መካከል የመዲናዋን የጤና መሰረተ ልማት ሽፋን እና አገልግሎትን የተመለከተው ይገኝበታል።

በመዲናዋ የጤና መሰረተ ልማት ተዳራሽነት ለማስፋት ከተማ አስተዳደሩ እያደረገ በሚገኘው እንቅስቃሴ ሆስፒታሎችን ከማደስ እና ከማሻሻል ባለፈ ሁለት አዳዲስ ሆስፒታሎች እየተገነቡ እንደሚገኝ ተገልጿል።

የጤና መድህን ፣ የመድሀኒት አቅርቦት እና የባለሙያዎችን ቁጥር ማሳደግ ላይ ከተማ አስተዳደሩ የሰራቸው ስራዎች በምክር ቤት አባላቱ አድናቆት ተችሯቸዋል። ይህ በእንዲህ እንዳለ የምክር ቤት አባላቱ ከማህበረሰቡ ጋር ባደረጉት ውይይት የጤና ጣቢያ እጥረት ያለባቸው አካባቢዎችን ችግር ለመቅረፍ ምን እንደታቀደ ተጠይቋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ በሰጡት ምላሽ በሁሉም ወረዳዎች ጤና ጣቢያ ከመገንባት ባለፈ የጥራት ደረጃቸውን ማሻሻል ላይ ትኩረት መደረጉን አንስተዋል።

ለአብነትም በ2017 በጀት አመት 9 ጤና ጣቢያዎች በመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ጥራት መመዘኛ ተሰርተው ለአገልግሎት ክፍት መሆናቸውን ተናግረዋል። በተጨማሪም 13 ሆስፒታሎች የታደሱ ሲሆን የዘውዲቱ እና የሚኒሊክ ሆስፒታልን ጨምሮ 4 ሆስፒታሎች ላይ ማስፋፍያ እና እድሳት እየተከናወነ እንደሚገኝ ከንቲባዋ ጠቁመዋል።

አዲስ አበባ በአለም ጤና ድርጅት መመዘኛ መሰረት የጤና ተደራሸነትን መልሳለች ያሉት ከንቲባ አዳነች፤ በቀጣይ የጥራት ደረጃን ማሻሻል እና መዲናዋን የሜዲካል ቱሪዝም ማዕከል ለማድረግ ትኩረት እንደሚሰጥ ለምክር ቤቱ አብራርተዋል።

በዳዊት በሪሁን

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review