ሀማስ በሕይወት የሚገኙ ሁሉንም ታጋቾች ለቀቀ

You are currently viewing ሀማስ በሕይወት የሚገኙ ሁሉንም ታጋቾች ለቀቀ

AMN – ጥቅምት 03/2018 ዓ.ም

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ለይፋዊ ጉብኝት እስራኤል በሚገኙበት ወቅት ሀማስ ሁሉንም በህይወት የሚገኙ ታጋቾች መልቀቁ ተዘግቧል።

ትራምፕ ባቀረቡት የሰላም ስምምነት የመጀመሪያ ምዕራፍ ላይ የተስማሙት እስራኤል እና ሀማስ የስምምነት ነጥቦችን በመተግበር ላይ ይገኛሉ።

ባሳለፍነው አርብ እስራኤል ወታደሮቿን ከጋዛ ማስወጣት ስትጀምር በዛሬው ዕለት ደግሞ ሀማስ ታጋቾችን ለቋል።

በቴልአቪቭ ታጋቾች አደባባይ፤ የታጋች ቤተሰቦች እና ሌሎች የከተማዋ ነዋሪዎች ተገኘተው ለታጋቾቹ አቀባበል አድርገዋል።

ከዚህ ባለፈም ህይወታቸው ያለፈ 26 የታጋቾች አስክሬን ሀማስ ለቀይ መስቀል አስረክቧል።

እስራኤል በበኩሏ ሴቶች እና ታዳጊዎችን ጨምሮ 2 ሺህ ፍልስጤማውያን የፖለቲከኛ እስረኞችን መልቀቋን ሮይተርስ ዘግቧል።

በእስራኤል ጉበኝት ላይ የሚገኙት የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ እስራኤል በጦርነት ያገኘችውን ድል ወደዘላቂ ሰላም መቀየር አለባት ሲሉ አሳስበዋል።

በእስራኤል ኬኔሴት (ፓርላማ) ደማቅ አቀባበል የተደረገላቸው ፕሬዝዳንቱ “የጋዛ ጦርነት ተጠናቋል፤ አሁን በመካከለኛው ምስራቅ ዘላቂ ሰላም ስለማስፈን ልንነጋገር ይገባል” ብለዋል።

የመጀመሪያው ምዕራፍ የስምምነቱ አካል በስኬት መጠናቀቁን ተከትሎ፤ ቀጣይ የጦርነቱን በዘላቂነት መቆም የሚበይኑ ወሳኝ የስምምነት ነጥቦች ተጠባቂ መሆናቸው ተነግሯል።

በተለይም ከጦርነቱ በኋላ ሀማስ ስለሚኖረው እጣ ፋንታ እና በጋዛ አስተዳደር ዙሪያ በሁለቱ ወገኖች መካከል ያለውን ሰፊ ልዩነት ማጥበብ ቀጣይ የቤት ስራዎች ናቸው።

በእስራኤል በኩል የፍልስጤም ሀገር ሆኖ መመስረትን ጉዳይ እንድትቀበል የተለያዩ አለምአቀፋዊ ጫናዎች በርትተዋል፤ በሁለቱ ወገኖች ዘላቂ ሰላም ለማስፈን የፍልስጤም ሀገር የመሆን ጥያቄ ምላሽ ማግኘት ይኖርበታልም ተብሏል።

በዳዊት በሪሁን

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review