የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሽዴ ከኩዌት የአረብ ኢኮኖሚ ልማት ፈንድ ዳይሬክተር ጋር ተወያዩ

You are currently viewing የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሽዴ ከኩዌት የአረብ ኢኮኖሚ ልማት ፈንድ ዳይሬክተር ጋር ተወያዩ

AMN-ጥቅምት 4/2018 ዓ.ም

የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሽዴ ከኩዌት የአረብ ኢኮኖሚ ልማት ፈንድ ተጠባባቂ ዳይሬክተር ጋር ተወያይተዋል።

ከዓለም ባንክና ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይኤምኤፍ ) ዓመታዊ ስብሰባ ጎን ለጎን ተጠባባቂ ዋና ዳይሬክተር ከሆኑት ወሊድ አል-ባሀር ጋር በኢትዮጵያና በኩዌት ፈንድ መካከል ያለውን የቆየ አጋርነት ማጠናከር ላይ ትኩረት ያደረገ ውይይት አካሄደዋል።

በውይይቱ የኢትዮጵያን የቅርብ ጊዜ የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች፣ በፈንዱ የገንዘብ ድጋፍ እየተደረገላቸው ያሉ ፕሮጀክቶችን እና የኩዌት የአረብ ኢኮኖሚ ልማት ፈንድ በኢትዮጵያ ያለውን ተሳትፎ ማሳደግ በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ መክረዋል።

የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ የመንግሥት ሰፋፊ ማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያዎችን የዕዳ ቅነሳ እና ኢትዮጵያ ቅድሚያ የምትሰጣቸውን ቁልፍ የልማት ዘርፎች አስረድተዋል።

ከዚህ ባለፈም የኩዌት የአረብ ኢኮኖሚ ልማት ፈንድ ኢትዮጵያ አዲስ የምታስገነባውን ግዙፍ ኤርፖርት ጨምሮ በግሉ ዘርፍ ልማት እና የትራንስፖርት መሠረተ ልማት ላይ ድጋፍ ሊያደርግ የሚችልበትን ሁኔታ አብራርተዋል።

የኩዌት የአረብ ኢኮኖሚ ልማት ፈንድ ዳይሬክተር አል-ባሀር የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ራዕይ እና በኢኮኖሚ ማሻሻያ ያስመዘገበችውን የመጀመሪያ ስኬቶች አድንቀዋል።

የኩዌት ፈንድ ለኢትዮጵያ ልማት በተለይም በትላልቅ የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶች ፋይናንስ እና በሌሎች ቅድሚያ በሚሰጣቸው ዘርፎች ድጋፍ ለማድረግ ያለውን ቁርጠኝነትም አረጋግጠዋል።

ሁለቱም ወገኖች አጋርነታቸውን ለማሳደግ እና የኩዌት ፈንድ ለኢትዮጵያ ስልታዊ እና ከፍተኛ ተጽዕኖ ላላቸው የልማት ፕሮጀክቶች የሚሰጠውን ድጋፍ ለማጠናከር መስማማታቸውን ከገንዘብ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

በዳዊት በሪሁን

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review