የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን እና የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አክሲዮን ማህበር በኢትዮጵያ የፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎች ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አድርገዋል።
በባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የስፖርት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ መኪዩ መሐመድ በተገኙበት ውይይት ላይ የተለያዩ አቅጣጫዎች ተቀምጠዋል፡፡
ፕሪምየር ሊጉ የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጋር በጋራ በወሰዱት ስምምነት መሠረት የሊግ ጨዋታዎች በአዲስ አበባ ስታዲየም እንዲካሄዱ መወሰኑ ተነስቷል፡፡
ጨዋታዎቹ በፍፁም ሰላማዊና ስፖርታዊ ጨዋነት በተላበሰ መልኩ እንዲካሄድ በውይይቱ አፅዕኖት ተሰጥቶበታል።
የ2018ዓ.ም የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ቅድመ ዝግጅት ጨዋታዎች ዙሪያ ውድድሩ የሚመራበት እና የፀጥታና የቴክኒክ ኮሚቴ እቅድ እንዲዘጋጅ ፣ ንዑሳን ኮሚቴዎች እንዲደራጁ፣ ለሁሉም የሊግ ክለቦች የቅድመ ዝግጅት ውይይት መደረግ እንዳለበትም ተጠቁሟል።
በየወሩ የሊጉ ጨዋታዎች የሚገመገሙበት ሁኔታ እደሚኖር አቅጣጫ የሰጡት የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የስፖርት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ መኪዩ መሐመድ ለሚመለከታቸው አካላት የግንዛቤ መስጫ መድረክ እንዲዘጋጅ አሳስበዋል፡፡
በውይይቱ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን፣ የኢትዮጵያ ፕሪሚየሊግ አክሲዎን ማህበር የቦርድ ሰብሳቢ፣ የፀጥታ ሀላፊዎች፣ የፌዴራል ፖሊስ ተወካይ፣ የሚኒስቴር መ/ቤቱ የስፖርት ልማት ዘርፍ መሪ ስራ አስፈፃሚዎች፣ የአዲስ አበባ ከተማ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ተወካይ ተሳትፈዋል።