የጡት ካንሰር ህመም – ምልክት፣ ህክምና እና መከላከያ ዘዴዎች

You are currently viewing የጡት ካንሰር ህመም – ምልክት፣ ህክምና እና መከላከያ ዘዴዎች
  • Post category:ጤና

AMN- ጥቅምት 5/2018 ዓ/ም

የጡት ካንሰር ሴቶችን በማጥቃት ከካንሰር ጋር ተያይዞ ለሚከሰት ሞት ዋነኛው መንስኤ መሆኑን በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ጥቁር አንበሳ ሆሲፒታል የቀዶ ጥገና ህክምና፣ የጡትና የኢንዶክራይን ረዳት ኘሮፌሰር የሆኑት ዶክተር ህይወት የሽጥላ ገልፀዋል።

ዶክተር ህይወት የሽጥላ ከኤ ኤም ኤን ዲጂታል ሚዲያ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደገለጹት በኢትዮጵያ በየዓመቱ 16 ሺህ የሚጠጉ ሴቶች በጡት ካንሰር ይያዛሉ ተብሎ እንደሚገመት ጠቁመው፣ በዓመት 9 ሺህ የሚሆኑ ሞቶች እንደሚመዘገቡም ገልፀዋል።

የእድሜ መጨመር፣ በቤተሰብ ውስጥ የጡት ካንሰር ታሪክ መኖር፣ ከመጠን ያለፈ ውፍረት፣ አልኮል መጠቀም፣ ሲጋራ ማጨስ፣ የወር አበባ ከሚመጣበት ጊዜ ቀደም ብሎ መምጣትና ዘግይቶ መቆም ለጡት ካንሰር አጋላጭ ከሆኑ ምክንያቶች መካከል ዋነኞቹ ናቸው ብለዋል፡፡

በጡት አካባቢ ህመም የሌለው እባጭ፣ በጊዜ ሂደት የሚመጣ የጡት ጫፍ ወደ ውስጥ መሰርጎድ፣ ከጡት ጫፍ የሚወጣ ደም የቀላቀለ ውሃ መሳይ ፈሳሽ መኖር፣ የጡት ቆዳ ቀለም መቀየር፣ ቁስለት መፍጠር እንዲሁም ከብብት ስር እብጠት መከሰት የጡት ካንሰር ምልክቶች መሆናቸውን ዶክተር ህይወት ገልፀዋል፡፡

ምንም ዓይነት ህመም ሳይኖር በየጊዜው የቅድመ ምርመራ ማድረግ፣ የጡት አልትራሳውንድ፣ ማሞግራፊ፣ የጡት ራጅ፣ የጡት ቀዶ ጥገና፣ የኬሞቲራፒ፣ የጨረር፣ የሆርሞን እንደአስፈላጊነቱ ከጡት ላይ ለተጨማሪ ምርመራ ናሙና በመውሰድ የጡት ካንሰር ህክምና ማድረግ እንደሚገባ ገልፀዋል፡፡

አንዲት ሴት እድሜዋ 2ዐ ዓመት ከደረሰ በኃላ በወር አንድ ጊዜ የወር አበባዋ መጥቶ ከሄደ ከ5 እስከ 7ኛው ቀን የራሷን ጡት በራሷ በመዳሰስ ጤንነቱን ማረጋገጥ ይኖርባታል ብለዋል፡፡

3ዐ ዓመት የሞላት ሴት ከሆነች ደግሞ ይህንን ከማድረግ በተጨማሪ ወደ የጤና ተቋማት በመሄድ በ1 ወይም በ2 ዓመት አንድ ጊዜ ቅድመ ምርመራ ማድረግ ይኖርባታል፡፡

የ40 ዓመት ዕድሜ ያላት ሴት በዓመት አንድ ጊዜ የቅድመ ምርመራ እና እንደአስፈላጊነቱም የማሞግራፊ ምርመራ በማድረግ የጡት ካንሰርን ከመከሰቱ በፊት ቀድሞ መከላከል ይችላል፡፡

በተጨማሪም የአኗኗር ዘይቤን ማስተካከል የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ፣ ጤናማ የሆኑ ምግቦችን መመገብ፣ ከመጠን ያለፈ ውፍረትን ማስወገድ እና የአልኮል መጠጦችን ማቆም ለካንሰር ህመም ተጋላጭነትን ይቀንሳል ሲሉ ዶክተር ህይወት የሽጥላ አብራርተዋል፡፡

በሀገር አቀፍ ደረጃ የጡት ካንሰር ሳይሰራጭ ወደ ጤና ተቋም የሚመጡ ሴቶች ከ30 በመቶ የማይበልጡ ሲሆን፣ ይህንንም ወደ 60 በመቶ ለማድረስ ታቅዷል፡፡

በኢትዮጵያ በ33 የህክምና ተቋማት የካንሰር ህክምና አገልግሎት እየተሰጠ ሲሆን፣ በ5 ጤና ተቋማት ደግሞ የጨረር ህክምናዎች እየተሰጡ እንደሚገኝ መረጃዎች ይጠቁማሉ።

በበረከት ጌታቸው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review