እንግሊዝ ለዓለም ዋንጫ ያለፈች የመጀመሪያዋ የአውሮፓ ሀገር ሆናለች።
ምድብ 11 ላይ የምትገኘው እንግሊዝ ላቲቪያን 5ለ0 በማሸነፍ የዓለም ዋንጫ ትኬቷን ቆርጣለች። ሀሪ ኬን (ሁለት) ፣ አንቶኒ ጎርደን ፣ ኤብሪቼ ኤዜ እና ቶኒሴቭስ በራሱ ላይ የሦስቱ አናብስትን ግቦች ከመረብ አሳርፈዋል።

110 የብሔራዊ ቡድን ጨዋታውን ያደረገው ሀሪ ኬን ያስቆጠራቸውን ግቦች 76 አድርሷል። እንግሊዝ ያደረገቻቸውን ስድስት ጨዋታ አንድም ግብ ሳይቆጠርባት ማሸነፍ ችላለች።
ምድብ ስድስት ላይ የተደለደለችው ፖርቹጋል ከሀንጋሪ ጋር 2ለ2 ተለያይታ ለዓለም ዋንጫ ማለፏን ሳታረጋግጥ ቀርታለች። የፖርቹጋልን ሁለት ግቦች ክርስቲያኖ ሮናልዶ በስሙ አስመዝግቧል።
ለሀንጋሪ አቲላዛላይ እና ዶሚኒክ ዞቦዝላይ ኳስ እና መረብ አገናኝተዋል። በሌሎች ጨዋታዎች ስፔን ቡልጋሪያን 4ለ0 ስታሸንፍ ፣ ጣልያን እስራኤልን 3ለ0 መርታት ችላለች።
በሸዋንግዛው ግርማ