የነባርና የአዲስ የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን የአባልነት ምዝገባ ከጥቅምት 1 እስከ ህዳር 30 2018 ዓ.ም በከተማዋ ንደሚካሄድ የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ አስታወቀ ።
የቢሮ ኃላፊው ዶክተር ዮሐንስ ጫላ ለመገናኛ ብዙሃን በሰጡት መግለጫ፤ በአዲስ አበባ ሁሉም ክፍለ ከተሞች ስር በሚገኙ ጤና ጣቢያዎች የ2018 ዓ/ም የነባርና አዳዲስ የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን የአባልነት ምዝገባ ከጥቅምት 1 እስከ ህዳር 30 እንደሚካሄድ ገልጸዋል ።
ጤና ጣቢያ በሌለባቸው አካባቢዎች የሚኖሩ የማህበረሰብ ክፍሎች በሚኖሩበት ወረዳ መመዝገብ እንደሚችሉም ገልጸዋል ።
በመዲናዋ በ2017 ዓ.ም ከ2 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ዜጎች የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን አባል መሆናቸውን የቢሮ ኃላፊው ገልፀው፤ አባላቶች እና ቤተሰቦቻቸው በተመላላሽ እና በተኝቶ ህክምና ከጤና ጣቢያ ጀምሮ ባሉት የመንግስት ጤና ተቋማት የጤና አገልግሎት ማግኘታቸውን ገልጸዋል ።
በ2018 ዓ.ም የነባር አባላትን እድሳት ለማካሄድና 10 በመቶ የሚሆኑ አዲስ አባላትን በመጨመር ከ2 ነጥብ 7 ሚሊዮን በላይ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ለማድረግ መታቀዱን ተናግረዋል፡፡
የመክፈል አቅምን ባገናዘበ መልኩ ለነባር አባላትና ለአዲስ ተመዝጋቢዎች ለምዝገባ ከ1 ሺህ 500 እስከ 10 ሺህ 500 ብር እንዲሁም የመመዝገቢያ 200 ብር መያዝ ይጠበቅባቸዋል ብለዋል፡፡
የቢሮ ኃላፊው የደሃ ደሃ ለሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች ደግሞ ወጪውን የከተማ አስተዳደሩ እንደሚሸፍን ተናግረዋል።
አዋጁን መሰረት በማድረግ የመክፈል አቅምን ያገናዘበ የማህበረሰብ ጤና መድህን መዋጮ ተግባራዊ መደረጉ ፍትሐዊ የጤና አገልግሎት ተደራሽነትን ለማረጋገጥ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑንም ገልጸዋል ።
በዳንኤል መላኩ