በምዕራብ ኦሮሚያ አካባቢዎች ግንባታቸው የተቋረጠና የተጓተቱ የመንገድ ፕሮጀክቶች በፍጥነት በማጠናቀቅ የህብረተሰቡን የልማት ጥያቄ ለመመለስ እንደሚሰራ የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር አስታወቀ፡፡
የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ከምዕራብ ኦሮሚያ አካባቢዎች የስራ ሀላፊዎች ጋር በአካባቢው የመንገድ ፕሮጀክቶች አፈፃፀም ላይ ያተኮረ ምክክር አድርጓል።
የአስተዳደሩ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ኢንጀነር መልካ በቀለ በወቅቱ እንዳሉት በምዕራብ ኦሮሚያ አካባቢዎች በተለያዩ ምክንያት ግንባታቸው የተቋረጡና የግንባታ አፈጻጸማቸው ዝቅተኛ የሆኑ መንገዶችን በፍጥነት በማጠናቀቅ ለአገልግሎት እንዲበቁ በትኩረት ይሰራል።
አሁን ላይ ግንባታቸውን በአጭር ጊዜ ለማጠቀቅ ሥራ ከሚጀመርባቸው አራት መንገዶች መካከል ሁለቱ ግንባታቸው የተጓተተ ሲሆን ቀሪዎቹ ደግሞ በተለያዩ ምክንያቶች ግንባታቸው ተቋርጦ የነበሩ መሆኑን አስረድተዋል።
የመንገድ ፕሮጀክቶቹን ግንባታ ለማስቀጠል መንግስት 6 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር በጀት መያዙን ተናግረው የመንገዶቹ ግንባታ በፍጥነት ለማጠናቀቅም ከዞኑ አስተዳደርና ከህብረተሰቡ ጋር በቅንጅት ይሰራል ብለዋል።
የመንገዶቹ ግንባታ ሲጠናቀቅ ከዚህ በፊት የነበረውን የትራንስፖርት እንቅስቃሴ ችግር ከመፍታት ባለፈ ለህብረተሰቡ ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ ምቹ ሁኔታ እንድሚፈጥር አመልክተዋል።
በብልጽግና ፓርቲ የምዕራብ ወለጋ ዞን ቅርጫፍ ጽህፈት ቤት ሀላፊ አቶ በዳሳ ዳባ፣ በዞኑ በነበረው የጸጥታ ችግርና በተለያዩ ምክንያቶች ግንባታቸው የተቋረጡ መንገዶችን መልሶ ለማስጀመር በሚደረገው ጥረት የዞኑ አስተዳደር አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚደርግ ገልጸዋል፡፡
በየደረጃው ያሉ የዞኑ አመራሮችም ለመንግዱ ግንባታ መፋጠን የድርሻቸውን እንዲወጡም አሳስበዋል፡፡
በመድረኩ ላይ የተሳተፉ የወረዳ አመራሮች በበኩላቸው ከለውጡ ዓመታት ወዲህ መንግስት የህዝቡን የልማት ተጠቃሚነት እያረጋገጠ መሆኑን ማንሳታቸዉን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
አሁን ላይ ግንባታቸው ተጀምሮ የተቋረጡና የተጓተቱ መንገዶችን ለማጠናቅቅ በሚደረገው ጥረትም ህብረተሰቡን የማስተባበር ሀላፊነታቸውን በአግባቡ እንደሚወጡም ገልጸዋል፡፡