የሶሪያ ፕሬዝዳንት አሕመድ አልሻራ ስልጣን ከያዙ ለመጀመሪያ ጊዜ በሩስያ ይፋዊ የስራ ጉብኝት እያደረጉ ይገኛሉ።
የሩስያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን አዲሱን ፕሬዝዳንት በሞስኮ ተቀብለው ያነጋገሩ ሲሆን፤ ሀገራቱ ግንኙነታቸውን ማስቀጠል በሚችሉባቸው ጉዳዮች ዙሪያ መክረዋል።
ለ13 አመታት በተካሄደው የሶሪያ የእርስ በእርስ ጦርነት በተቃራኒ ጎራ ተሰልፈው የነበሩት ሁለቱ መሪዎች ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን ለማስቀጠል ተስማምተዋል።
ከአምስት አስርት አመታት በላይ በደማስቆ የዘለቀው የአሳድ አስተዳደር እንዲገረሰስ ውጊያ ሲጀመር ሩስያ እና ኢራን ከበሽር አላሳድ መንግስት ጎን ቆመው የአሁኑን የሀገሪቱን ፕሬዝዳንት ጦር ወግተዋል።
ከዚህ ባለፈም የአሳድ መንግስት ውድቀት ሲረጋገጥም ፕሬዝዳንቱ ቤተሰባቸውን ይዘው የሸሹትም ወደ ሞስኮ እንደሆነ ይታወቃል ሲል ኒውዮርክ ታይምስ አስነብቧል።
በሞስኮ እና በደማስቆ መንግስታት መካከል ከ1944 ጀምሮ የነበረው ወዳጃዊ ግንኙነት ቀጣይነቱ እንደማይቋረጥ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ገልጸዋል።
የሶሪያው ፕሬዝዳንት አሕመድ አልሻራ በበኩላቸው ሶሪያን መልሶ ለመገንባት በሚደረገው ጥረት የሞስኮ ሁለንተናዊ እገዛ ያስፈልገናል ነው ያሉት።
በምግብ አቅርቦት እና በሶሪያ የሀይል ማመንጫዎች ላይ ሩስያ ያላት ተጽእኖ አሁንም ከፍተኛ መሆኑን አርቲ አስነብቧል።
ለሁለት ሰዓታት በዘለቀው የሁለቱ መሪዎች ውይይት በመድሀኒት እና ስንዴ አቅርቦት ፣ በኢነርጂ እና ትራንስፖርት እንዲሁም በቱሪዝም ዘርፎች ላይ ያላቸውን ግንኙነት ለማጠናከር ተስማምተዋል።
ከዚህ ባለፈም በውጥረት ውስጥ በሚገኝው የመካከለኛው ምስራቅ ቀጠና ሰላም ለማስፈን በሚደረገው ጥረት ሩስያ በሚኖራት ሚና ላይም መሪዎቹ መክረዋል።
በዳዊት በሪሁን