ታማኝ ግብር ከፋዮች አዲስ አበባ እንደገና እንድትሰራ ማድረጋቸውን የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አቶ አገኘሁ ተሻገር ገልፀዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር “ግብር ለሃገር ክብር” በሚል መሪ ቃል ለታማኝ ግብር ከፋዮች የእውቅና እና ሽልማት መርሃ ግብር አካሂዷል፡፡
በመርሃ ግብሩ በክብር እንግድነት የተገኙት የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አቶ አገኘሁ ተሻገር፤ መንግስት ሃገሪቱ መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሃገራት ተርታ እንድትሰለፍ የተለያዩ ዕቅዶችን ነድፎ እየተገበረ መሆኑን በመጥቀስ፤ ለዚህም የገቢ ሰብሳቢ ተቋማት ኢኮኖሚው ከሚያመነጨው ሀብት በቂ ገቢ ለመሰብሰብና ሀገራዊ የልማት ዕቅዶችን ለማሳካት እየሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።
መንግስት በሃገር ውስጥ ከሚፈጠረው ሃብት የከተሞች ዕድገት እና የዜጎች የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን እያረጋገጠ መሆኑን አቶ አገኘሁ ተሻገር ተናግረዋል፡፡
በቀጣይም የዜጎችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በተለይ የአዲስ አበባ ከተማን የዕድገት ፍላጎት ለማሟላት የመንግስት እና የግብር ከፋዩ ማህበረሰብ ይበልጥ ተቀናጅቶ መስራት እንደሚያስፈልግ ጠቅሰዋል፡፡
የሃገራችንን ዕድገት ለማረጋገጥ እና የከተማ አስተዳደሩን ገቢ የመሰብሰብ ዓቅም ይበልጥ ለማሳደግ ሊሰራ እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡
በአሁኑ ጊዜ በአዲስ አበባ ከተማ የሚታየው ሁለንተናዊ ለውጥ ያለ ታማኝ ግብር ከፋዮች ተሳትፎ አይሳካም ያሉት አቶ አገኘሁ አዲስ አበባ ከተማ እንደገና እንድትሰራ አድርጋችኋልና ለዚህም ከፍተኛ ምሰጋና ይገባችኋል ሲሉ አድናቆታቸውን ችረዋል ፡፡
የከተማ አስተዳደሩ አመራሮች፤ በተለይ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ለከተማዋ ዕድገት እንዲሁም አዲስ አበባ የአፍሪካ ምሳሌ እንድትሆን ለሚያደርጉት ጥረት መንግስት ከፍተኛ አድናቆት አለው ያሉት አፈ-ጉባኤ አቶ አገኘሁ ተሻገር፤ የተጀመረው የለውጥ ጉዞ እንዲቀጥል ለግብር ከፋዩ መሰረታዊ የአገልግሎት አሰጣጥ እና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን በየጊዜው እየፈተሹ መሰራት ሁሌም የትኩረት ማዕከል ሊሆን ይገባዋል ሲሉ አሳስበዋል፡፡
በያለው ጌታነህ
