ሰሜን አሜሪካ ፣ ካናዳ እና እንግሊዝን ጨምሮ በተለያዩ የዓለም ሀገራት የተከናወነው የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር ምዕራፍ በስኬት መጠናቀቁን የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አስታውቋል።
ኮሚሽኑ በደቡብ አፍሪካ ፣ በሰሜን አሜሪካ ፣ በካናዳ ፣ በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ፣ በስዊድን እና በእንግሊዝ ስኬታማ የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር ምዕራፍ ማከናወኑ ተገልጿል።
የኮሚሽኑ ቃል አቀባይ አቶ ጥበቡ ታደሰ በሰጡት መግለጫ በስድስቱ ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን እና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ያለምንም ገደብ በነፃነት ሃሳባቸውን ስለመግለፃቸው ተናግረዋል።
ከዲያስፖራው የማህበረሰብ ክፍል በርካታ ጥያቄዎች ተነስተዋል ያሉት ቃል አቀባዩ፤ የተለየ አቋም ያላቸው ዜጎችም የተሳተፉበት ሂደት እንደነበር ገልፀዋል።
ተሳታፊዎች ሀገራዊ መግባባት ሊደረሰባቸው ይገባል ያሏቸውን አጀንዳዎች ለኮሚሽኑ ማቅረባቸውንም ቃል አቀባዩ አስታውቀዋል።
አሁንም በምክክር ሂደቱ ያልተሳተፉ የዲያስፖራ ማህበረሰብ አባላት በበይነ መረብ የመሳተፍ አማራጭ እንዳላቸው ጠቁመዋል።
በትግራይ ክልል አሁንም ምክክር ለማካሄድ አስቻይ ሁኔታዎች ለመፍጠር ስራዎች እየተሰሩ እንደሚገኝ በመግለጫው ተነስቷል።
በወንድምአገኝ አበበ