የሰላም ጸር በመሆን የሚንቀሳቀሰው ጽንፈኛ ቡድን የጥፋት እቅድ በህዝቡ እና በጸጥታ ሃይሉ ትብብር መክኗል

You are currently viewing የሰላም ጸር በመሆን የሚንቀሳቀሰው ጽንፈኛ ቡድን የጥፋት እቅድ በህዝቡ እና በጸጥታ ሃይሉ ትብብር መክኗል

AMN ጥቅምት 7/2018

የሰላም ጠንቅ በመሆን የሚንቀሳቀሰው የጽንፈኛ ቡድኑ የጥፋት እቅድ በህዝቡ እና በጸጥታ ሃይሉ ትብብር መምከኑን የወልዲያ ከተማ አስተዳደር ሠላምና ጸጥታ መምሪያ አስታወቀ።

በአማራ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች የሚንቀሳቀሰው ጽንፈኛ ቡድን የህዝብ ሰላም እንዲናጋና ማህበራዊ እንቅስቃሴዎች እንዲስተጓጎሉ ለማድረግ የሚጥር መሆኑ ይታወቃል።

ጽንፈኛ ቡድኑ ዓላማ እገታና ዘረፋ ከመፈፀም ባለፈ የትምህርትና መሰል ማህበራዊ ተቋማትን አገልግሎት ማሰናከልና የማውደም እቅድ በመያዝ ሲንቀሳቀስ ቆይቷል።

ቡድኑ ከኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ተልዕኮ በመቀበል በክህደት ሀገርና ህዝብን የመጉዳት ዓላማ ይዞ እየሰራ መሆኑም ይታወቃል።

በመሆኑም የዚህን ጽንፈኛ ቡድን አላማ በቅጡ በመረዳት በህዝቡና በጸጥታ ሃይሉ ትብብር የህግ ማስከበርና ሰላምን የማጽናት ስራ በተጠናከረ መልኩ ቀጥሏል።

ከዚሁ ጋር በተገናኘ በሰሜን ወሎ ዞን ወልዲያ እና አካባቢው ያለውን ነባራዊ ሁኔታ በተመለከተ ኢዜአ የወልዲያ ከተማ አስተዳደር ሠላምና ጸጥታ መምሪያ ኃላፊ ኮማንደር ደርበው አዳነ ጋር ቆይታ አድርጓል።

ኃላፊውም በማብራሪያቸው የሰላም ጠንቅ በመሆን የሚንቀሳቀሰው የጽንፈኛ ቡድኑ የጥፋት እቅድ በህዝቡና በጸጥታ ሃይሉ ትብብር እየመከነ መሆኑን አንስተው ህግ የማስከበር ስራው ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑንም አረጋግጠዋል።

የጽንፈኛ ቡድኑ ዓላማ ግድያና ዘረፋ ከመፈፀም ባለፈ ወጣቶች ወደ ትምህርት ቤት እንዳይሄዱ፣ አርሶ አደሮች ሰርተው እንዳያመርቱና ማህበራዊ እንቅስቃሴ እንዲገደብ መሆኑን አንስተው የህዝብን ሰላም ለማረጋገጥ የህግ ማስከበር እርምጃ የግድ መሆኑን አንስተዋል።

በዚህም መሰረት በጸጥታ ሃይሉ ጠንካራ እርምጃ እና በህዝቡ ትብብር ህግ የማስከበር ስራ መከናወኑን አስታውሰው በዚህም በወልዲያና አካባቢው አስተማማኝ ሰላም መኖሩን ኮማንደር ደርበው ገልጸዋል።

በወልዲያና አካባቢው ያለውን ሰላም በዘላቂነት ለማስቀጠልም ከወጣቶች፣ ከሀገር ሽማግሌዎች፣ ከኃይማኖት አባቶችና ከተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች ተወካዮች እንዲሁም ጋር በቅርበት እየሰራን ነው ብለዋል።

የወልዲያና አካባቢውን ሰላም ለማጽናት የጸጥታ ኃይሎች በተቀናጀ መንገድ እየሰሩ መሆኑን አንስተው የከተማዋ ነዋሪዎችም በብሎክ በመደራጀት ለሰላም ዘብ መሆናቸውን በተግባር አረጋግጠዋል ብለዋል።

ከከተማዋ ነዋሪዎች መካከል ድንቁ ወልደሰንበት እና ጀማል አህመድ፤ የሰላም ማጣት ለብዙ ውስብስብ ችግሮች እንደሚዳርግ ያየነው በመሆኑ ለሰላም ግንባታ ማንኛውንም ዋጋ ለመክፈል ዝግጁ ነን ሲሉ ማረጋገጣቸዉን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ለዘላቂ ሰላም ግንባታ የመንግስትን የሰላም ጥረት አድንቀው በጥፋት መንገድ በቀጠለው ጽንፈኛ ቡድን ላይ የተጠናከረ እርምጃ ሊወስድ ይገባል ብለዋል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review