ከሚጠፉ ግለሠቦች የአፋልጉኝ ማስታወቂያዎች ላይ ስልክ ቁጥሮችን በመውሰድ ገንዘብ አስገቡ በሚሉ ግለሠቦች ላይ ጥብቅ ምርመራ መጀመሩን የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ አስታወቀ፡፡
በተለያዩ ጊዜያት ከቤተሰቦቻቸው የሚጠፉ ህጻናት፣ ታዳጊዎችና ጎልማሶች ወላጆቻቸው፣ አሳዳጊዎቻቸው ወይም ቤተሰቦቻቸው ጉዳዩን ወደ ፖሊስ ከመውሰድ ይልቅ በተለያዩ መንገዶች የአፋልጉኝ ማስታወቂያዎችን እንደሚለቁ ይታወቃል።
በማህበራዊ ሚዲያዎች ከሚለቀቁ የአፋልጉኝ ማስታወቂያዎች ላይ ከሚጠፉ ግለሰቦች ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት የሌላቸው አንዳንድ ግለሰቦች ” ልጃችሁ ወይም የጠፋው ሰው እኛ ጋ ነው ገንዘብ አስገቡ፤ ይህን ካላደረጋችሁ በህይወት አታገኟቸውም” በማለት በርካታ ገንዘብ በባንክ እንዲገባላቸው ያደረጉ ግለሰቦች ላይ ፖሊስ በጥናት የተደገፈ የወንጀል ምርመራ ተግባር ጀምሯል።
ወላጅ የልጁን ወይም የቤተሰብ አባሉን መጥፋት ለፖሊስ ካሳወቀም ሊሞቱብን ይችላሉ በሚል ጉዳዩን ወደ ፖሊስ ይዞ ከመምጣት ይልቅ ገንዘብ ለጠየቁ፣ በዚህ የወንጀል ተግባር ላይ ለተሠማሩና ለተደራጁ ወንጀል ፈጻሚዎች ገንዘብ እያስገባ ለተለያዩ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውሶች እየተጋለጠ እንደሚገኝ እየተደረጉ ባሉ የምርመራ ስራዎች ተረጋግጧል።
ለአብነት ያህል የ15 ዓመቱ አምረላህ ናስር ጥቅምት 01 ቀን 2018 ዓ/ም ከኮልፌ ቀራንዮ ክ/ከተማ ልዩ ስሙ አባጃሌ ተብሎ ከሚጠራው አካባቢ ጠፍቶ በአካባቢው ከሚገኝ አንድ መስኪድ ሊገኝም ችሏል።
ቤተሰብም ልጃቸው ቢገኝም ባሠራጩት የአፋልጉኝ ማስታወቂያ ላይ ስልክ ቁጥር ያገኙ ግለሰቦች ልጃችሁን ከፈለጋችሁ 50ሺህ አስገቡ በማለት ለቤተሰብ ስልክ መደወላቸውን ለፖሊስ ገልጸዋል።
ሌላዋ ታዳጊ ማርያና መድሀንየ ሠለሞን መስከረም 16 ቀን 2018 ዓ/ም ከምትኖርበት ቦሌ ክ/ከተማ ወረዳ 4 ልዩ ቦታው ዝማም ሆቴል አካባቢ ከሚገኝ መኖሪያ ቤታቸው የጠፋች ሲሆን እናት ልጃቸው መጥፋቷን በማህበራዊ ሚዲያ ሲያፈላልጉ ቆይተው የለሚ ኩራ ክ/ከተማ ፖሊስ መምሪያም ፍለጋ በማድረግ ታዳጊዋን መስከረም 24 ቀን 2018 ዓ/ም ከቤተሰብ ጋር አገናኝቷል።
ከታዳጊዋ መጥፋት ጋር ግንኙነት የሌላቸው ግለሰቦች ልጅቷን በህይወት የምትፈልጉ ከሆነ ገንዘብ አስገቡ ማለታቸውን የታዳጊዋ ቤተሰቦች ለፖሊስ ገልጸዋል።
ሌላኛው ታዳጊ ዳግም አሸብር ጥቅምት 5 ቀን 2018 ዓ/ም የካ ክ/ከተማ ወረዳ 5 ልዩ ቦታው ኮከበጽባህ ትምህርት ቤት አካባቢ ከሚገኝ መኖሪያ ቤቱ መጥፋቱን ቤተሰቦቹ በማህበራዊ ሚዲያ እንዲለቀቅ አድርገዋል።
ነገር ግን ፖሊስ የቀረበለትን አቤቱታ መነሻ አድርጎ ባደረገው ክትትልም ታዳጊውን ከአጎቱ ቤት ማግኘቱን ቢያገኝም ከልጁ መጥፋት ጋር ምንም ግኑኙነት የሌላቸው ግለሰቦች ቤተሰብ ጋር በመደወል ልጁን በህይወት የምትፈልጉት ከሆነ 100ሺህ ብር አስገቡልን ማለታቸውን ቤተሰብ ገልጿል።
ፖሊስ እነዚህንና መሠል አቤቱታዎችን ተቀብሎ ተገቢውን ምርመራ እያደረገ ሲሆን ገንዘብ እንዲገባላቸው የጠየቁ፣ ገንዘብ የገባላቸውና ከዚህ ወንጀል ጋር ግንኙነት ያላቸው ግለሰቦች ላይ ጥብቅ ምርመራ መጀመሩን አስታዉቋል፡፡
ህብረተሰቡ አብዛኛውን ጊዜ ተመሳሳይ ችግሮች ሲያጋጥሙት ጉዳዩን ወደ ማህበራዊ ሚዲያ ከማምጣት ይልቅ ህግን ተከትሎ ለፖሊስ በማመልከትና ምርመራ እንዲጀመር በማድረግ ራሱን ከወንጀል ፈጻሚዎች እንዲጠብቅ የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ ለኤኤምኤን በላከዉ መረጃ መልእክቱን መልዕክቱን ያስተላልፋል።