የውሃ ውስጥ በረከት

You are currently viewing የውሃ ውስጥ በረከት

 ንጋት ሐይቅ በተፈጥሯዊ የዓሣ ማምረት ዘዴ ብቻ በዓመት እስከ 10 ሺህ ቶን ዓሣ የማምረት አቅም እንዳለው ተገልጿል

“ዓሣ አበላሻለሁ ዓባይ ዳር ነው ቤቴ፤ ዶሮ መረቅማ ከወዴት አባቴ” በሚለው የድምጻዊ አሰፋ አባተ ዜማ ውስጥ በግጥም ስር የተሸሸጉ እልፍ ቁምነገሮች አሉ፡፡ ለዛሬ ሁለቱን እናንሳ። ወንዝ ዳር፣ ሐይቅ ዳር አሊያም ባህር ዳር …  ያለ ሰው፣ ዓሣ አይቸግረውም የሚለው አንዱ ነው። ሌላውና ልብ ልንነው የሚገባው ጉዳይ ደግሞ  “ዶሮ መረቅማ ከወዴት አባቴ” የምትለው ስንኝ  ውስጥ የተቀመጠው ጭብጥ ነው፡፡ በሆነ ነገር የዶሮ መረቅ ከዓሣ እንደሚበልጥ ይነግረናልና፡፡

በርግጥ በፕሮቲን ይዘታቸው ከፍ ማለት ምክንያት እንደ ዓሣዎቹ ዝርያና ሁኔታ አሊያም እንደ ዶሮዎቹ አይነት አንዱ አንዱን እየተካ ቢበላለጡም ዓሣን የመሰለ  ግብዣ ቢያስደስት ነው እንጂ የሚያስቆጭ አይደለም፡፡ ዓሣ መመገብ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው የሥነ ምግብ እና የጤና ባለሙያዎች ደጋግመው ይመክሩናል፤ የተለያዩ ጥናቶችም ይህንን እውነት ይመሰክሩልናል፡፡

ለዚህ ደግሞ ግድቦቻቸውን አሊያም የውሃ ሃብቶቻቸውን ለተለያዩ ጉዳዮች ከመጠቀም ባሻገር ዓሣን በማርባትና በመመገብ ጠንካራ ባህል ያላቸው ሀገራት ስላገኙት ከፍ ያለ ፋይዳ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ንጋት ሐይቅ ላይ በመንፈስ አረፍ ብለን እንመለከታለን፡፡

በሰሜን ምስራቅ እስያ የምትገኘው ጃፓን በባህር የተከበበች ድንቅ ምድር ናት፡፡ ይህ ደግሞ ዓሣን ከባህላዊ ምግቦቿ አንዱ እንዲሆን አድርጎታል። ጃፓናውያን ዓሣን  ‘koi’ ወይም ፍቅር እያሉ ይጠሩታል፡፡ እንደ ጃፓን ቱደይ ዘገባ አንድ ጃፓናዊ በቀን ከ30 ግራም በላይ ዓሣ ይመገባል፡፡

ፖርቹጋል ከአውሮፓ ከፍተኛ ዓሣ ከሚመገቡ ሀገራት መካከል አንዷ ናት። አማካኝ ዓመታዊ ፍጆታ በአንድ ሰው 57 ኪሎ ግራም ነው፡፡ በተመሳሳይ ኖርዌይ ዓሣን በብዛት ከሚመገቡ ሀገራት ተጠቃሽ ናት፡፡ በዓመት በነፍስ ወከፍ ከ50 ኪሎ ግራም በላይ ዓሣ ለምግብነት ይውላል፡፡ በተለይም በተማሪዎች የምሳ ዕቃ ውስጥ፣ በህሙማን መጠየቂያ ማዕድ ውስጥ እንዲሁም በታላላቅ ብሔራዊ በዓላት በክብር የሚበላ ጣፋጭና ተመራጭ ምግብ ነው፤ ዓሣ፡፡

ይህም ብቻ ሳይሆን ኖርዌይ ዓሣን ኤክስፖርት በማድረግ በዓመት ዳጎስ ያለ ገቢ ታገኝበታለች፡፡ ለአብነትም እ.ኤ.አ. 2024 የባህር ምግቦችን ወደ ውጭ በመላክ 175 ነጥብ 4 ቢሊዮን ኖክ (NOK) ማግኘቷን የኖርዌይ የባህር ምግቦች ምክር ቤት እ.ኤ.አ ጥር 2024 ይፋ ያደረገው መረጃ ያመለክታል፡፡

እንደ ምክር ቤቱ መረጃ ከሆነ ሀገራት የውሃ ሃብታቸውን ለዓሣ እርባታ በመጠቀም ከሚያገኙት ምጣኔ ሀብታዊ ጠቀሜታ ባሻገር ጤናማ፣ ንቁ፣ የፈጠራ ክህሎትን የታደለ እና የተረጋጋ ማህበረሰብ  መፍጠር ችለዋል፡፡

ዓሣን መመገብ ባህላቸው ካደረጉ እና በኢኮኖሚና መሰል ጉዳዮች ተጠቃሚ ከሆኑ ሀገራት መካከል ደቡብ ኮሪያ፣ ህንድ እና ቻይናን የመሳሰሉ ሀገራት ተጠቃሽ ናቸው፡፡ በተለይም እንደ ህዳሴ ግድብ ያሉ የንጋት ሐይቅን የመሳሰሉ ግድቦቻቸውን በመጠቀም  ለሀገር ውስጥ የምግብ ፍጆታ ብቻ ሳይሆን ለውጭ ገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ የሆኑ ሀገራትን በዋቢነት ማንሳት እንችላለን፡፡

ግድቦቻቸውን ለኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫነት፣ ለመስኖ፣ ጎርፍን ለመከላከል፣ ለመጠጥ ውሃ አቅርቦት፣ ለቱሪዝምና መሰል ነገሮች ከመጠቀማቸው ባሻገር የምግብ ዋስትናቸውን ጭምር ማረጋገጥ የቻሉ ሀገራት እንዳሉ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ነሐሴ 2020 በታተመው “Water Management for Sustainable Food Production” በተሰኘው መፅሐፍ ላይ ሰፍሯል፡፡

በመፅሐፉ ላይ እንደሰፈረው በ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ ከመጣው የህዝብ ቁጥርና ፍላጎት አንፃር ዓለም የምግብ ምርትን ከ70 በመቶ በላይ የማሳደግ ፈተና ተጋርጦበታል። በተለይ ዘላቂነት ያለው የምግብ ምርት ለማግኘት ግድቦችን በብዙ መልኩ ለምርትና ምርታማነት መጠቀም ይገባል፡፡

በሌላ በኩልም በምግብ እህል ራስን ከመቻል አንፃር ሀገራት የውሃ ሀብት አስተዳደርና አጠቃቀማቸውን በትኩረት ሊመለከቱ እንደሚገባም በመፅሐፉ ሰፍሯል፡፡ አንዳንድ ሀገራት ደግሞ ግድቦቻቸውን ለዓሣ እርባታ እና የምግብ ፍጆታን በሚሸፍኑ ልማቶች ላይ በስፋት በማዋል የበለጠ ተጠቃሚ እንደሆኑም ተመላክቷል፡፡

ለአብነትም በደቡብ-ምስራቅ ባንግላዲሽ በራንጋማቲ አውራጃ ውስጥ በካርናፉሊ ወንዝ ላይ ያለው የካፕታይ ግድብ እ.ኤ.አ በ1962 የተገነባ ነው። ይህ የካፕታይ ሐይቅ ግድብ 58 ሺህ 300 ሄክታር ይሸፍናል፡፡ 9 ሜትር ጥልቀትና 36 ሜትር ከፍታም አለው። ባንግላዲሽ ከዚህ ግድብ በምታገኘው የዓሣ ምርት በአመዛኙ የሀገር ውስጥ የምግብ ፍጆታዋን ትሸፍናለች፡፡

ለልዩ ልዩ ጉዳዮች የሰራቻቸውን ግድቦች ለዓሣ ምርት ጭምር በመጠቀም ከፍተኛ ለውጥ ካመጡ ሀገራት መካከል ህንድ አንዷ ናት፡፡ የዓለም የምግብ ድርጅት መረጃ እንደሚያመለክተው ህንድ ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚውሉ 19 ሺህ በላይ ግድቦች አሏት፡፡ በዓመትም 93 ሺህ 650 ቶን ዓሣ በአማካኝ ታመርታለች፡፡ በዚህም ለበርካቶችም የስራ ዕድል ከመፍጠሯና የውጭ ምንዛሬ ጭምር ከማግኘቷ ባሻገር የምግብ ፍጆታዋንም ትደጉምበታለች፡፡

በሌላ በኩል ብራዚል ብዙ ትላልቅ የውሃ ማጠራቀሚያዎች ያሏቸው ትላልቅ የሃይድሮ ኤሌክትሪክ ግድቦች አሏት። በግድቦቹ የተፈጠሩት ሐይቆች ሙሉ በሙሉ ጥቅም ላይ ሲውሉ 3 ነጥብ 5 ሚሊዮን ቶን ዓሣ በዓመት የማምረት አቅም አላቸው፡፡

ቴላፒያ የተሰኘው ዓሣ ለውጭ ገበያ በጣም ተፈላጊ ሲሆን፣ ብራዚል እ.ኤ.አ በ2021 ወደ 10 ቶን የሚጠጋ ዓሣ ወደ ውጭ ልካለች፡፡ የብራዚል ዓሣዎችን በዋናነት ከሚገዙ ሀገራት መካከል ዩናይትድ ስቴትስ፣ ኮሎምቢያ እና ቻይና መሆናቸውን ሳኦ ፖሎ የሚገኘው የብራዚል አረብ ንግድ ምክር ቤት የዜና ጣቢያ (ANBA) ሰሞነኛ መረጃ ያመላክታል፡፡

በሌላ በኩል ቻይና፣ ኖርዌይ፣ ቬትናም፣ ህንድ፣ ቺሊ፣ ኢኳዶር፣ ታይላንድ፣ አሜሪካ፣ ሩሲያና ኢንዶኔዥያ እ.ኤ.አ በ2024 እና 2025 የዓሣ ምርትን በስፋት ለዓለም ገበያ ያቀረቡ ሀገራት ሲሆኑ ዋና ምንጫቸውም ግድቦቻቸውን በአግባቡ በመጠቀማቸው እንደሆነ ዓለም አቀፉ የንግድ መረጃዎች ምንጭ የሆነው ትሬድ ኢንዴክስ (TradeImeX) እ.ኤ.አ ሚያዚያ 3 ቀን 2024 ይፋ ያደረገው መረጃ ያመላክታል፡፡

ይህንን ሀቅ ይዘን ወደ ራሳችን ስንመለስ ከኢትዮጵያ ፈልቆ ሜዳና ተራራውን ፈልቅቆ፣ ለም አፈሯን እየጠራረገ የሚነጉደው የዓባይን ወንዝ በረከት በመጠቀም ካርቱምና ካይሮን በመሳሰሉ ከተሞች የዓሣ ቋንጣ በርካሽ ይቸበቸባል። አያሌዎችንም ከርሃብ ይታደጋል፡፡

ግብፅ ከዓባይ ወንዝ በየዓመቱ ከ650 ሺህ ቶን ዓሣ በላይ ታመርታለች፡፡ ይህ ከፍተኛ ምርት ዓሣ በተመጣጣኝ ዋጋ ለገበያ እንዲቀርብና የምግብ ዋስትና እንዲረጋገጥ ከፍተኛ ድርሻ አለው። በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ግብፃውያን የተመጣጠነ ምግብ እንዲያገኙ አስችሏቸዋል፡፡ ይህንን እውነት በዝርዝር መመልከት ካሻዎ የኬኒያ ዕለታዊ ጋዜጣ ቢዝነስ ዴይሊ እ.ኤ.አ ታህሳስ 2020 (River Nile’s innovative fish farms feed millions) በሚል ርዕስ ይፋ ያደረገውን መረጃ ይመልከቱ፡፡

የዓባይን ወንዝ የዓሣ ሀብት እያሰብን ወደ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ስናመራ ብዙ በረከቶችን እናገኛለን፡፡ ይሄውም ከህዳሴው ግድብ መጠናቀቅ ጋር ተያይዞ በአካባቢው 1 ሺህ 680 ስኴር ኪሎ ሜትር ስፋት ባለው መሬት ላይ በአማካኝ 44 ሜትር ጥልቀት ያለውና 74 ቢሊዮን ሜትር ኪዮብ ውሃ የመያዝ አቅም ያለው ሰው ሰራሽ ሐይቅ ተፈጥሯል፡፡

በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ የግብርና ኮሌጅ የእንስሳት ሳይንስ ትምህርት ክፍል ፕሮፌሰር ዮሴፍ ተክለ ጊዮርጊስ በ2010 ዓ.ም በአፍሪካና በኢትዮጵያ ሐይቆች ላይ ያደረጉት ጥናት እንደሚያመላክተው የህዳሴው ግድብ ሰው ሰራሽ ሐይቅ (ንጋት ሐይቅ) ከስፋቱና ውሃ ከመያዝ አቅሙ አንፃር በተፈጥሯዊ የዓሣ ማምረት ዘዴ ብቻ በዓመት እስከ 10 ሺህ ቶን ዓሣ የማምረት አቅም ይኖረዋል፡፡ በተለይም ዘመናዊ የዓሣ እርባታ ዘዴን በመተግበር የንጋት ሐይቅን ዓሣ የማምረት አቅም ከዚህ በብዙ እጥፍ ማሳደግ  እንደሚቻልም መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

በእርግጥም እንደ ንጋት ሐይቅ ባሉ የውሃ ሃብቶቻችን ዓሣ የማምረት አቅማችንን በአግባቡ ስንጠቀም፣ የአመጋገብ ባህላችንን ከዓሣ ጋር ስናዛምደው ከላይ እንደ ጠቃቀስናቸው ጃፓን፣ ቻይና እና መሰል ሀገራት ለስራ፣ ለፈጠራ የተጋ እና የተረጋጋ ማህበረሰብን ለመገንባት እና ሀገርን በሁለንተናዊ መልኩ በፅኑ መሰረት ላይ ማንበር እንችላለን።      

በመለሰ ተሰጋ

  

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review