አቶ ሙጅብ ሰኢድ “ግብር ለሀገር ክብር” በሚል መሪ ቃል የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባዘጋጀው የታማኝ ግብር ከፋዮች የእውቅናና ሽልማት መርሃ ግብር ላይ ተሸላሚ ከነበሩ የመዲናዋ ታማኝ ግብር ከፋዮች መካከል አንዱ ናቸው።

ለተከታታይ አምስት አመታት የታማኝ ግብር ከፋይነት እውቅናና ሽልማት ማግኘታቸውን አቶ ሙጅብ ሰኢድ ከኤ ኤም ኤን ጋር በነበራቸዉ ቆይታ ገልፀዋል፡፡
አቶ ሙጂብ ስለግብር መክፈል ሲያስረዱ፤ ሀቀኝነት የህሊና ሰላም እንደሚሰጥ፤ ግብር መክፈልም ጸጋ እና መታደል መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ከቅርብ አመታት ወዲህ በመዲናዋ በተሰሩ የልማት ስራዎች በአጭር ጊዜ ውስጥ ከፍተኛ ለውጥ መመዝገቡንም ተናግረዋል፡፡
የአዲስ አበባ መንገዶች በኮሪደርና ወንዝ ዳርቻ ልማት ስራዎች በመለወጣቸዉና ዘመናዊነትን በመላበሳቸዉ ከአሁን ቀደም የማዉቀዉ አካባቢ ግራ አጋብቶኝ ከአንዴም ሁለቴ መንገድ ጠፍቶብኛል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
በስራ ምክንያት የተለያዩ የአለም ከተሞችን የማየት እድል እንደነበራቸው የተናገሩት አቶ ሙጂብ፤ አዲስ አባባ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከዓለም ከተሞች ጋር በመፎካከር ላይ እንደምትገኝም ጠቁመዋል፡፡

ልማትና እድገቱን ስመለከት በታማኝ ግብር ከፋይነቴ ኮርቻለሁ፤ ግብር መክፈል ያስደስታል ኩራትም ነዉ ሲሉ ገልጸዋል፡፡
ግብር በታማኝነት በመክፈላችን የሀገራችንን ልማት በታማኝነት አሳልጠን ትሩፋቱን ለሌሎቹ የህብረተሰብ ክፍሎችም ማጋራት ችለናል ብለዋል።

ይህ ተግባር ትልቅ ደስታ እና እርካታ እንደሚሰጣቸው የገለፁት አቶ ሙጂብ፤ በቀጣይም መሰል እድሎችን ለማግኘት እንደሚሰሩ አመላክተዋል።
ለታማኝ ግብር ከፋዮች እንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት ያስተላለፉት ተሸላሚው፤ ሌሎች ግብር ከፍዮችም የሚጠበቅባቸውን ግብር በአግባቡ በመክፈል ጤናማ ውድድር እንዲያደርጉ እና ለሃገራቸው ልማት የበኩላቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል
በፍሬሕይወት ብርሃኑ