ቴክኖሎጂን በአግባቡ ጥቅም ላይ ማዋል ለተሻለ ኢኮኖሚያዊ እድገት መነቃቃት እድል ፈጥሯል
ዜጎች በመነገድ፣ ቤትና ንብረት በማከራየት፣ ዕውቀታቸውን በመሸጥ ወይም በሌላ በማንኛውም መንገድ ከሚያገኙት ገቢ ላይ በህግ በተቀመጠው አግባብ ግብር መክፈል ይጠበቅባቸዋል። በሕግና በአሠራር በተቀመጠው መሰረት ግብር መክፈል የሚጠበቅባቸው ግብር ከፋዮች ለመንግስት የመክፈል ግዴታ አለባቸው፡፡ ግብር ሰብሳቢው መንግስት ደግሞ የሰበሰበውን የግብር ገቢ ለሀገር ልማትና ዕድገት እንዲሁም ለህብረተሰቡ ተጠቃሚነት የሚያገለግሉ መሰረተ ልማቶችን ይገነባል፤ በፍትሃዊነትም ያዳርሳል፡፡ ፈጣንና ቀልጣፋ የመንግስት አገልግሎትን ያቀርባል፡፡ ትምህርትና ጤናን በጥራት እና በስፋት ያዳርሳል፡፡ የሀገር ሠላምና ሉዓላዊነት ያስከብራል፡፡ ሌሎችንም ሀገራዊ ሥራዎችን ይፈፅማል፤ ያስፈፅማል፡፡
የግብር ሰብሳቢ ተቋማት ከግብር አሰባሰብ ጋር በተያያዘ ድርብ ኃላፊነት አለባቸው፡፡ አንደኛው ከግብር ከፋዮች ተገቢውን ግብር በወቅቱ የመሰብሰብ ኃላፊነት ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ ለግብር ከፋዮች ፈጣንና ቀልጣፋ የሆነ አገልግሎት መስጠት ነው፡፡ ከዚህ አንጻር በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቢሮ እየተሠራ ያለውን ሥራ ለመቃኘት እንሞክራለን፡፡
አቶ አብዱላዚዝ ከሊፋ፤ በአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ የኢንፎርሜሽንና ቴክኖሎጂ ዳይሬክተር ናቸው፡፡ እሳቸው እንደሚያስረዱት፤ ቢሮው የግብር(ታክስ) ገቢ አሰባሰብ ስርዓቱን ለማዘመን በቴክኖሎጂ የታገዘ አሠራርን እየተገበረ ነው፡፡ ለደረጃ “ሐ“ ግብር ከፋዮች ግብር የሚከፍሉበት በቴክኖሎጂ የተደገፈ (ኢ-ታክስ) ስርዓት፣ የገቢ አሰባሰብ መረጃ መላላኪያ ቴክኖሎጂ (ኢ- ረቨኑ ፕላን) ስርዓት፣ የነጻ ስልክ መስመር 7075፣ የእዳ ክትትል ስርዓት (ኢ- ፔይመንት እና ኢ- ፊሊንግ) ቴክኖሎጂዎች በአገልግሎት ላይ ውለው እየተሠራባቸው ነው፡፡
በተጨማሪም፤ የደረጃ “ሐ“ ግብር ከፋዮች የግብር ውሳኔ በ7075 አማካይነት በአጭር የጽሑፍ መልዕክት በስልካቸው እንዲደርሳቸው ይደረጋል፡፡ እነሱም በደረሳቸው አጭር የጽሑፍ መልዕክት መሰረት ባሉበት ሆነው ቴሌ ብር፣ ሲ ቢ ኢ ብር፣ ሞባይል ባንኪንግ በመሳሰሉት ዘመናዊ የክፍያ አማራጮች የሚከፍሉበት ሁኔታ ተመቻችቷል፡፡
አቶ አብዱላዚዝ አያይዘውም፤ የቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች አገልግሎት አሰጣጥን ለመከታተል፣ ለመደገፍ እና ለማሻሻል እንዲቻል ከማዕከል ሆኖ እያንዳንዱን መረጃ በፍጥነትና በጥራት የሚያደርስ የሰርቪላንስ ካሜራ ለአገልግሎት በቅቷል፡፡ ተቋሙ የመደባቸው የቁጥጥር ሠራተኞች ተገቢውን አገልግሎት በሕጋዊና አሠራሩን በጠበቀ መልኩ እንዲሰጡ፣ ግብር ከፋዩ ማህበረሰብም እንዳይጭበረበር እና ላልተገባ ጉዳት እንዳይዳረግ ለእነዚህ የቁጥጥር ሠራተኞች ማንነታቸውን በቀላሉ ለማወቅ የሚያስችል ባር ኮድ የተካተተበት መታወቂያ ተዘጋጅቷል፡፡ እንዲሁም በሂደት ላይ የሚገኙ የቀጥታ ቪዲዮ፣ የድምፅ ማስተላለፍ እና አካባቢን መከታተል ቴክኖሎጂዎችን ተግባራዊ ማደረግ መቻላቸው በግብር አሰባሰብ ሂደቱ ላይ ትልቅ አሻራ ስለማኖራቸው ገልፀዋል፡፡
ዓለም አቀፍ የገቢ ግብር እና ልማት ማዕከል (International center for tax and development) የተሰኘው ተቋም በ2020 እ.ኤ.አ ባወጣው መረጃ መሰረት የግብር ከፋይ ቁጥር መጨመር የሀገር ጠቅላላ ገቢን እንደሚያሳድግ ጠቁሟል። ከግብር ከፋዩ ዜጋ የሚሰበሰበው ገንዘብ ለጤና፣ ለትምህርት መስፋፋት እንዲሁም ፍትሃዊ የአኗኗር ዘይቤ እንዲኖር ያግዛል። ይህ መረጃ እንደሚያመላክተው ከመጀመሪያው የዓለም ጦርነት ማግስት የግብር አከፋፈል ስርዓትን በአግባቡ ለመተግበር የሚያስችለውን መመሪያ በአስገዳጅ የህግ ማዕቀፍ በማካተት ተግባራዊ ያደረጉት ምዕራባውያኑ አሁን ላይ ለሚታየው ዕድገትና ብልፅግናቸው ቁልፍ አስተዋፅኦ አድርጓል፡፡ ዜጎቻቸውም ለምን ግብር እንደሚከፍሉ ጥልቅ ግንዛቤ በመያዝ ያለማንም ቀስቃሽና ጎትጓች በወቅቱ ገቢ የሚያደርጉበትን ዕድል ፈጥሮላቸዋል፡፡
ሀገራት ከግብር የሚሰበሰበውን ገቢ በአግባቡ ለመሰብሰብ እንዲሁም ጥቅም ላይ እንዲውል ለማስቻል የተለያዩ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን በማልማት ጥቅም ላይ አውለዋል፡፡ ከዚህ አንፃር በአፍሪካ እንደ ኬንያ፣ ግብፅ፣ ቱኒዚያ እና ደቡብ አፍሪካ የመሳሰሉት ሀገራት ውጤታማ እንቅስቃሴ እያደረጉ ስለመሆናቸው፤ “እ.ኤ.አ በ2025 የተሻለ ሀገራዊ ገቢ ያገኙ 10 የአፍሪካ ሀገራት” በሚል ርዕስ ኤክስፖርት ፎከስ አፍሪካ የተሰኘው ድርጅት ይፋ ያደረገው መረጃ ይጠቁማል፡፡ በመረጃው ላይ እንዳሰፈረው በተለይ ጎረቤት ሀገራት ጠንካራ የኢኮኖሚ መሰረታቸውን የጣሉት ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን በግብር አሰባሰቡ ሂደት ላይ ተግባራዊ ማድረግ በመቻላቸው እንደሆነም ተጠቅሷል፡፡
ሀገረ ኬንያ ካላት የሕዝብ ቁጥር አንፃር አብዛኛውን ማህበረሰብ ተደራሽ ለማድረግ አይ – ታክስ ስርዓትን ተግባራዊ አድርጋ እየሠራች ትገኛለች፡፡ የአሰራር ስርዓቱ ሙሉ ለሙሉ ትኩረቱን የሚያደርገው በኦንላይን የግብር ከፋዮች ምዝገባ ከማካሄድ አንስቶ የግብር አሰባሰብ ሂደቱን ከወረቀት ንክኪ ነፃ በማድረግ ፤ ለብልሹ አሰራር እንደ ምክንያት የሆኑትን አካሄዶች መዝጋት ላይ ትኩረቱን ያደረገ ነው፡፡ ክፍያዎችንም በእጅ በሚገኙ ስልኮችና ላፕቶፖች አማካኝነት ይፈፅማሉ፡፡
በመዲናችን አዲስ አበባም የገቢ ግብር አሰባሰብ ሂደቱን የተሻለ ለማድረግ በተሠራው ሥራ ተጨባጭ ውጤቶችን ለማስመዝገብ ስለመቻሉ አቶ አብዱላዚዝ አስረድተዋል፡፡ በተለይ ከገቢ ግብር አሰባሰብ ሂደቱ ጋር ከ2010 በጀት ዓመት ጀምሮ በነበሩት የለውጥ ዓመታት የገቢ ዕድገቱ ትልቅ እምርታዊ ለውጥ ለማስመዝገብ መቻሉን ጠቅሰዋል። ለማሳያነትም በ2010 ዓ.ም 33 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር ተሰብስቦ የነበረ ሲሆን፤ በ2017 በጀት ዓመት እንደ ቢሮ ከ163 ቢሊየን ብር እንደ ከተማ ደግሞ 233 ቢሊየን ብር መሰብሰቡን አስረድተዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቢሮ በ2017 በጀት ዓመት 163 ቢሊዮን ብር ገቢ ሰብስቧል፡፡ ይህ ገቢ ከዓመቱ ዕቅድ አንፃር ብልጫ ያለው ሲሆን፤ አፈፃፀሙ 103 ከመቶ በመሆን ተመዝግቧል፡፡ ከቢሮው ያገኘነው መረጃ እንደሚያመላክተው ባሳለፍነው በጀት ዓመት በየሩብ ዓመቱ የነበረው አፈፃፀም ዕድገት ያሳየ ነበር፡፡ እንደመረጃው ከሆነ በ2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ቢሮው የሰበሰበው ገቢ መጠን 35 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ነበር። በሁለተኛው ሩብ ዓመት ደግሞ የተረሰበሰበው ገቢ መጠን 76 ቢሊዮን ብር ደርሷል። በሦስተኛው ሩብ ዓመት ወይም በበጀት ዓመቱ ዘጠነኛ ወር ላይ ቢሮው የሰበሰበው ገቢ መጠን 125 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡ ቢሮው ገቢ የማሰባሰብ ሥራውን በማጠናከር በበጀት ዓመቱ መጨረሻ ላይ የሰበሰበውን ጥቅል ገቢ 163 ቢሊዮን ብር አድርሷል፡፡
እንዲህ ያለውን የገቢ እቅድ አፈፃፀም ዕድገት ማሳካት የተቻለበትን ምክንያት ዳይሬክተሩ ሲያስረዱ፤ ያልተነኩ የገቢ መሰረቶችንና አቅሞችን በመለየት ገቢን አሟጦ ለመሰብሰብ ጥረት በመደረጉ፣ የታክስ ከፋዩ ሕብረተሰብ የህግ ተገዢነት ግንዛቤ ደረጃው ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱ፣ በገቢ ሰብሳቢው ተቋሙ የነበሩ በተለይም የአደረጃጀት፣ የአሠራር፣ የቴክኖሎጂና የሰው ኃይል አቅም እያደገና እየተሻሻለ በመምጣቱ ነው ብለዋል፡፡
“ቴክኖሎጂን በአግባቡ ጥቅም ላይ ማዋል ለተሻለ ኢኮኖሚያዊ እድገት መነቃቃት እድል ይፈጥራል” የሚሉን አቶ አብዱላዚዝ፤ ሀገራችን የጀመረቻቸውን በቴክኖሎጂ የተደገፈ አሠራር ተጠናክሮ መቀጠል ለነገ የሚባል ተግባር አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡ በተለይ ጳጉሜ 5 ቀን 2017 ዓ.ም. ተመርቆ ለአገልግሎት የበቃው የአዲስ መሶብ የአንድ ማዕከል ዲጂታል የመንግስት አገልግሎት ለመዲናዋ ነዋሪዎች ሁሉን አቀፍ አገልግሎት በአንድ ቦታ እንዲያገኙ ያግዛቸዋል፡፡ በማዕከሉ ግንባር ቀደም አገልግሎት ከሚሰጡ ተቋማት መካከል አንዱ የሆነው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቢሮም ሙሉ ዝግጅቱን አጠናቅቆ ወደ ስራ መግባቱን ጠቅሰዋል፡፡
አንድና ከዚያ በላይ አገልግሎቶችን በአንድ ማዕከል መስጠት መቻል ባለጉዳዮችን ካለምንም እንግልት ጉዳያቸውን እንዲፈፅሙ ያስችላል። በተለይም ደግሞ እንደ አዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ አገልግሎት አሰጣጥ ስርዓታችንን በቴክኖሎጂ ማስደገፍ መቻሉ ትልቅ አበረታች ተግባር ያደርገዋል፡፡ አንድ ባለሙያ በመስኮት ሆኖ ባለጉዳዮችን በምን አይነት ቀልጣፋ አገልግሎት ለማስተናገድ ችሏል የሚለውን የስታንዳርድ መለኪያ አለ፡፡ ይህ አሠራር ውጤታማነት እንዲረጋገጥ የቅርብ ክትትልና ድጋፍ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል፡፡
መዲናችን አዲስ አበባ እለት ተዕለት የምታሳየው ለውጥ፤ አይደለም በሀገር ውስጥ የሚኖረውን ዜጋ ቀርቶ የውጭ ሀገራት እንግዶቻችንን ጭምር አስገርሟል፡፡ በተለይም አዲስ አበባን የሚመጥኑ ፕሮጀክቶች በተፈለገው ሰዓት ተጠናቅቀው ለተጠቃሚዎች ክፍት የመሆናቸው ሚስጥር ደግሞ ታማኝ ግብር ከፋዮቿ ብሎም በጎ ፍቃደኛ ባለሃብቶቿ ገቢ የሚያደርጉትን ገንዘብ ተከትሎ ነው፡፡
እንደ ዳይሬክተሩ ገለፃ፤ አብዛኛው ቴክኖሎጂዎቻችን በሀገር ውስጥ ባለሙያዎቻችን የለሙ መሆናቸውን ተከትሎ ለአሰራር ሂደቱም ቢሆን ትልቅ እፎይታን ፈጥሯል፡፡ ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም መቻል በተጨባጭ ያስገኘውን ውጤት በተመለከተ አቶ አብዱላዚዝ እንዳስረዱት በአግባቡ የተተነተኑ መረጃዎችን ለማቅረብ ተችሏል። ግልፀኝነትና ተጠያቂነት የታከለበት የአሰራር ስርዓትን በመከተል ሌብነትና ብልሹ አሰራርን ለማስቀረት የቻለ ሪፖርት እንደየፈርጁ አዘጋጅቶ ለማቅረብ ስለመቻሉ ተገልጿል፡፡ ግብር ከፋዩ ማህበረሰብ በታማኝነት ግብር ለመክፈል ፍላጎት ማሳየት ችሏል፡፡
በተሠሩ የተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች አማካኝነት ግብር የምከፍለው የሀገር ፍቅር ስሜት ስላለኝ ነው እንዲሉ ለማድረግ ተችሏል፡፡ የተለያዩ የልማት ስራዎችን ከዳር ለማድረስ የታማኝ ግብር ከፋዩ ሚና እጅግ የላቀ ያደርገዋል፡፡ ከሃብት አንፃር ለወረቀት ይወጣ የነበረውን ወጪ በማስቀረት ወረቀት አልባ አገልግሎትን እንደ ባህል በመውሰድ የተሰራው ስራ እጅግ አስደሳች ያደርገዋል፡፡
በተጨማሪም ማህበረሰባችን ካለምንም መንገላታትና ጊዜ ማባከን ወዲያው ጉዳዩን ጨርሶ እንዲንቀሳቀስ ያግዘዋል፡፡ በተለይ በቴክኖሎጂ የተደገፈ የገቢ አሰባሰብ ሥርዓት የአሠራር ወጥነት፣ ፍጥነትና ወጪ ቆጣቢነትን በማስፈን ከለውጡ ሂደት ጋር የሚመጣጠን የገቢ አቅምን እንደሚፈጥር ለማስተዋል ስለመቻሉ አቶ አብዱላዚዝ ለዝግጅት ክፍላችን አስረድተዋል፡፡
በሄለን ጥላሁን