አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ በሚያሰራጫቸዉ የይዘት ስራዎች ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር ተያይዘዉ የሚነሱ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን እና ቅሬታዎችን ለመቅረፍ የጀመረዉን ስራ አጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ዋና ሥራ አስፈፃሚው አቶ ካሳሁን ጎንፋ ገልፀዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት የፍትህና መልካም አስተዳደር ቋሚ ኮሚቴ የአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክን የ2018 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት አፈፃጸምን ገምግሟል፡፡
ቋሚ ኮሚቴ ላነሳቸዉ ሃሳቦችና አስተያየቶች ማብራሪያ የሰጡት የአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ካሳሁን ጎንፋ፤ በግማገማዉ የተነሱት አጠቃላይ ሃሳቦች ተቋሙን ለበለጠ ስራ የሚያነሳሱና ተጨማሪ አቅም የሚፈጥሩ መሆናቸዉን አንስተዋል፡፡

ተቋሙ ቋሚ ኮሚቴው በተለያዩ ጊዜአት የሚሰጡትን ሃሳብና አስተያየቶቸ በመቀበልና ተግባራዊ በማድረግ እመርታዊ ለዉጥ እያስመዘገበ እንደሚገኝም ገልጸዋል፡፡
ዘመኑ የድህረ እዉነት ዘመን መሆኑን ያነሱት ዋና ስራ አስፈጻሚዉ፤ አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ በሚያሰራጫቸዉ የይዘት ስራዎች የተዛቡ መረጃዎችን ለማረምና ለማስተካከል ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል፡፡

ተቋሙ በመንግስትና በህዝብ ተሳትፎ በመዲናዋ እየተሰሩ የሚገኙና የከተማዋን ገጽታ ከፍ ያደረጉ የኮሪደርና የወንዝ ዳርቻ የልማት ስራዎችንና ሜጋ ፕሮጀክቶችን ጨምሮ የተለያዩ የሰላምና የልማት ስራዎችን ተደራሽ በማድረግ ሃላፊነቱን እየተወጣ እንደሚገኝም ዋና ስራ አስፈጻሚዉ ተናግረዋል፡፡
አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ “የትውልድ ድምፅ” በሚል መርህ እየሰራ እንደመሆኑ፣ ትምህርት በቴሌቪዥን ላይ መሥራቱ ይህንኑ የሚያረጋግጥ ነው ብለዋል፡፡
ዋልታ ረገጥ እሳቤዎችን ከመግራትና ህብረብሄራዊ አንድነትን ከማረጋገጥ ረገድም ገዢ ትርክቶች እንዲጠናሩ በማድረግ ለሌሎች ምሳሌ የሚሆኑ በርካታ የይዘት ስራዎችን በመተግበር ላይ እንደሚገኝም የኤ ኤም ኤን ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ካሳሁን ጎንፋ ገልጸዋል፡፡

አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ዋርካ እና አገልጋይ የተሰኙ የቀጥታ ስርጭት የምርመራ ዘገባዎችን ጨምሮ በተለያዩ ቋንቋዎች በሚያሰራጫቸዉ የዜና ፤ ትምህርታዊና የመዝናኛ ዝግጅቶች የህዝብ ድምፅ ሆኖ እያሰራ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡
አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ በመዲናዋ፤ በሃገር አቀፍና በአለም አቀፍ ደረጃ ቀዳሚ የመረጃ ምንጭ ለመሆን በአዲሱ አመት በአዳዲስ ይዘቶችና አቀራረቦች በርካታ የይዘት ስራዎችን ተደራሽ በማድረግ ላይ እንደሚገኝ የጠቆሙት ዋና ስራ አስፈጻሚዉ ብቁ የሰዉ ሃይልና አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ጭምር የጀመረዉን ስራ አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡
በብዝሃ ቋንቋ ተደራሽ ለመሆን እየሰራባቸው ካሉ 5 የሀገር ውስጥ እና 2 የውጭ ቋንቋዎች በተጨማሪ፣ ሌሎች ቋንቋዎች ለመጨመር እየሰራ እንደሚገኝም የኤ ኤም ኤን ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ካሳሁን ጎንፋ ጠቁመዋል፡፡
በታምራት ቢሻው