ከበጎ ልብ የሚፈልቅ በጎነት   

You are currently viewing ከበጎ ልብ የሚፈልቅ በጎነት   

በበጎ ፍቃድ አገልግሎት ጥሩ ተሳትፎ ያለው ሰው ጤናማ ህይወትን ለመምራት አያዳግተውም”                                                                                                                                                                                                                                   የስነ ልቦና አማካሪ ማስረሻ ገ/መድህን (ዶ/ር)

ወይዘሮ አልማዝ ገብረየስ ይባላሉ፡፡ በጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 2 ነዋሪ ናቸው። እድሜያቸውም በሃምሳዎቹ መጀመሪያ አካባቢ ነው፡፡ በማህበራዊ ኃላፊነቶች ላይ በንቃት የመሳተፍ ልምድም አላቸው፡፡ የትራፊክ እንቅስቃሴን በማስተናበር ሥራ ላይ ያዘወትራሉ፡፡ ለዚህ ምክንያታቸው ደግሞ፤ በተለምዶ ሽሮሜዳ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ የሚገኘው እንጦጦ አምባ ትምህርት ቤት ፊት ለፊት የደረሰ አስከፊ የትራፊክ አደጋ የፈጠረባቸው ስሜት ነው፡፡

በሽሮ ሜዳ እና በአካባቢው ላይ የሚንቀሳቀሱ እግረኞች እና አሽከርካሪዎች የትራፊክ ህግና መርህን በጠበቀ እና ስነ ምግባርን በተላበሰ ሁኔታ የመንገድ መሰረተ ልማትን እንዲጠቀሙ በሚያደርጉት የበጎ አድራጎት ሥራ አበረታች ግብረ መልስ እንደሚሰጧቸው ወይዘሮ አልማዝ ይናገራሉ፡፡ ታዛዥ እንደሚሆኑላቸው ጭምር ገልፀዋል። በኮሪደር ልማት አማካኝነት የተለዩ የእግረኛ፣ የሳይክል እንዲሁም የመኪና መንገዶች ለአገልግሎት መብቃታቸው የትራፊክ እንቅስቃሴው ወደ ጥሩ መስመር እንዲገባ አድርጓል፡፡ በእነዚህ መሰረተ ልማቶች ሁሉም እንደየፈርጁ አውቆ እንዲጠቀምባቸው እና የእለት ተዕለት ልምድ እንዲያደርገው የበኩላቸውን ኃላፊነት እየተወጡ እንደሚገኙ ጭምር አብራርተዋል፡፡

ወይዘሮ አልማዝ በዚህ አገልግሎታቸው ከጉለሌ ክፍለ ከተማ የህብረተሰብ ተሳትፎና በጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ዕውቅና ተሰጥቷቸዋል፡፡ ይህ ዕውቅና ለበለጠ አገልግሎት አነሳስቶአቸው ሠላሳ የሚሆኑ በጎ ፍቃደኛ ተማሪዎችንና ወጣቶችን በማሰባሰብ፣ አስፈላጊውን ዝግጅት በማድረግ እና ስልጠና እንዲወስዱ በማመቻቸት በክረምቱ ወቅት እንዲያገለግሉ ማድረጋቸውንም ገልፀዋል፡፡

“ከማህበረሰቡ የሚሰጠን አስተያየት እንድንበረታታ እና በይበልጥ እንድንሠራ ያደርገናል” የሚሉት ወይዘሮዋ፤ ልዩ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ወገኖች ቅድሚያ መስጠትን እንደመርህ በመያዝ የሚተገብሩት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ዋና የአስፋልት መንገድ መሻገር የሚፈልጉ አካል ጉዳተኞችን የተለየ ድጋፍ በማድረግ እያስተናገዱ ሲሆን ከእነዚህ የሕብረተሰብ ክፍሎች የሚያገኙት ምላሽ እና ምርቃት ከስጋ አልፎ ነፍስ ድረስ የሚዘልቅ መሆኑንም አልሸሸጉም፡፡ 

“በጎነት ለራስ የሚከፈል መስዋዕትነት ነው፡፡ እኛም አቅማችን ሲከዳን፣ ጤናችን ሲጓደል ቤታችንን የሚያቃናልን፣ መንገድ የሚያሻግረን ያስፈልገናል፡፡ የምንሠራው ሥራ የሚያስገኝልን የህሊና እርካታ እንዲህ በቀላሉ የሚገለጽ አይደለም፡፡ ልክ ቤታችን ገብተን አረፍ ስንል፣ ያሳለፍነውን በጎ ቀን በማሰብ ፈገግ ብለን እንድናመሽ፤ አዳራችንም ሰላማዊና የደስታ እንዲሆን ይረዳናል” ሲሉ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ያለው ፋይዳ በዋጋ የማይተመን መሆኑን አብራርተዋል፡፡

በአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 01 ነዋሪ የሆነው ወጣት ለማ ታደሰ፤ በተለያዩ የበጎ ፍቃድ ሥራዎች ላይ ተሳትፎ የማድረግ ልምድ አለው፡፡ በተለይ በቤት እድሳት ላይ ላለፉት አራት ዓመታት ጉልበቱን ሳይሰስት ተሳትፏል፡፡ እሱ በተሳተፈባቸው በጎ ሥራዎች አማካኝነት 16 የሚሆኑ የአቅመ ደካማ ቤቶች ዕድሳት ተደርጎላቸው ለተጠቃሚዎች መተላለፋቸውን ያስታውሳል፡፡ ይህንን መሰል ተግባር ላይ በመሳተፉ ከፍተኛ የሕሊና እርካታ እንደሚሰጠው ጠቁሟል።

ወጣት ለማ እንደገለፀው፤ በ2017 የክረምት የበጎ ፈቃድ መርሃ ግብር ሙሉ ጊዜውን የአቅመ ደካሞችን ቤት በማደስ፣ በትራፊክ  ማስተናበር እንዲሁም በደም ልገሳ መርሃ ግብር ላይ ለመሳተፍ ችሏል። በበጋ መርሃ ግብር ላይ እንዲሁ ይህንኑ ተግባር አጠናክሮ ለመቀጠል ተዘጋጅቷል። በጎ ተግባር በመስራት ውስጥ የሚገኘው የህሊና ሰላም የትኛውንም ተግባር ከውነን ከምናገኘው እርካታ በእጅጉ የላቀ ነው፡፡

በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ላይ ሲሳተፍ ያገኘነው አዳጊ እድሜው በአስራዎቹ መጀመሪያ ላይ የሚገኝ ነው። ሳንድሮ ቢንያም ይባላል፤ በማይ ሊትል ጂ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ውስጥ የ5ኛ ክፍል ተማሪ ነው፡፡ ስድስት ኪሎ አካባቢ በትራፊክ ማስተናበር እና በአረንጓዴ ተክሎች እንክብካቤ ላይ ጥሩ ተሳትፎ ያደርጋል፡፡ የዘንድሮውን ክረምትም በዚሁ መርሃ ግብር ነው ያሳለፈው፡፡ በበጋው መርሃ ግብር እንዲሁ ከትምህርት ቤት መልስ ከቀኑ 10 ሰዓት ጀምሮ እስከ ምሽት 12 ሰዓት ድረስ እግረኞች በእግረኛ መንገድ እንዲጓዙ እና ለሳይክል ተብሎ በተለዩ ስፍራዎች ላይ እንዳያቋርጡ የማድረግ ሥራ ይሠራል፡፡

በእድሜ ገፋ ያሉ አባቶችን እና እናቶችን እንዲሁም አካል ጉዳተኞችን በሚያሻግርበት ወቅት የተለያዩ ምርቃቶችን እንደሚመርቁት ተናግሯል። በተለይ “ትምህርትህን ይግለፅልህ፤ ያሳድግህ፤ ለትልቅ ደረጃ ያብቃህ” የሚል ምርቃት ሲቀበል በእጅጉ ደስታ እንደሚፈጥርለት ነግሮናል፡፡

አስተያየት ሰጪዎቹ አገልግሎቱን በሚያከናውኑበት ጊዜ ምርቃት እንደሚያገኙ የተናገሩትን የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎችም ያጠናክሩታል፡፡ ለዚህ የወጣት ቢንያም  የሺጥላ አስተያየት ሁነኛ ማሳያ ነው፡፡

ወጣት ቢንያም፤ ነዋሪነቱ በጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 2 ነው፡፡ ከሽሮ ሜዳ ወደ ስድስት ኪሎ ዩኒቨርሲቲ  የሚወስደውን መንገድ ብዙ ጊዜ ይጠቀማል፡፡ የአይን ብርሃኑን ያጣ ሲሆን ከቤት ሲወጣ ብዙ ጊዜ የሚያሳስበው መኪና መንገድ እንዴት እንደሚያቋርጥ ነው። ታድያ የመኪናውን መንገድ ለማቋረጥ የሚቸገርባቸው ጊዜዎች ቢኖሩም፤ በጎ ፍቃደኞች በቦታው ላይ ካሉ ይህ ስጋቱ እና መቸገሩ እንደሚቀረፍለት ተናግሯል። ብዙን ጊዜ ለእንቅስቃሴ በሚጠቀምበት ከስድስት ኪሎ ሽሮሜዳ ያለው የመንገድ መስመር ላይ በጎ ፍቃደኞች ወይም በጎነትን የተላበሱ ሠዎች ስለማይጠፉ፤ መንገድ ለመሻገር መፈለጉን በነገራቸው ቅፅበት እገዛቸውን እንደሚያደርጉለት ገልጿል፡፡ በበጎ ተግባር ላይ የተሰማሩ ሰዎች ለኛ አካል ጉዳተኞች ሁነኛ መፍትሄ ሆነውልናልም ብሏል፡፡

“መንገድ በማቋርጥበት ወቅት በሚያደርጉልኝ እገዛ ምክንያት ልቤ እርፍ ይላል፡፡ ለዚህም በምላሹ እኔን እንዳሳረፉኝ እግዚያብሔር እነሱንም በቸገራቸው ነገር ላይ እረፍት ያለው ነገር እንዲሰጣቸው እመርቃቸዋለሁ” ብሏል፤ ወጣት ቢኒያም፡፡ እነርሱ የሚሠሩት በጎ ሥራ ውጤታማ እንዲሆን ሌላውም ታዛዥ እና ቀናኢ መሆን እንዳለበትም መልዕክቱን አስተላልፏል፡፡

ለመሆኑ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ላይ የሚሳተፉ በጎ ፍቃደኞች በሚከውኑት ተግባር ምን አይነት የስነ ልቦና ፋይዳ ያገኛሉ? ስንል ለስነ ልቦና አማካሪ ማስረሻ ገ/መድህን (ዶ/ር) ጥያቄ አንስተናል፡፡

እሳቸው በምላሻቸው እንዳብራሩት፤ “አንድ ሰው ማህበረሰብን የሚጠቅም ስራ በሰራው ልክ ወደር የሌለው የአእምሮ እርካታ እንዲጎናፀፍ እድል ይፈጥርለታል። በጎ ሥራ አልያም ማህበረሰቡን የሚጠቅም ሥራ ለመሥራት እራስን ዝግጁ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ አንድ ሰው አቅሙ እንደፈቀደለት በገንዘብ መደገፍ ባይችል እንኳን በጉልበቱ ማገዝ ይችላል። የአቅመ ደካሞችን ቤታቸውን ከማደስ በዘለለ የአረጋውያንን ጽዳት በመጠበቅ እና መሰል ስራዎች ማህበረሰቡን የሚጠቅም ስራ መሥራት ይቻላል፡፡

ቁጥራቸው ቀላል የማይባል ወጣቶች ብዙ ጊዜያቸውን በአልባሌ ቦታዎች ላይ በመገኘት፣ እራሳቸውን እና ቤተሰባቸውን በማይጠቅም ተግባር ላይ ያሳልፋሉ። ምን አልባትም ዓመታትን በትምህርት አሳልፈው ቤተሰብ ብሎም ሀገር ከእነርሱ ብዙ በሚጠብቅበት ወቅት መልሶ ተረጅ የሚሆኑበት ሁኔታ ይታያል፡፡ ይህ ደግሞ  ኪሳራ አለው” የሚሉት ማስረሻ (ዶ/ር)፤ በተቻለ መጠን ትምህርት ካለቀ በኋላ ሥራን ሳይንቁ ተግቶ መሥራትን ከመልመድ በተጨማሪ ወገንን በማሰብ በበጎ ፍቃድ ተግባራት ላይ መሠማራት ይገባል፡፡ ይህን ማድረግ መቻል ደግሞ ጥቅሙ ለራስ ጭምር መሆኑን መገንዘብ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡

“በበጎ ተግባራት ላይ መሳተፍ በዋናነት የሚያስገኘው ጥቅም የህሊና እርካታ ነው። በተለይ አንድ ሰው በእንደዚህ ባለ ተግባር ላይ ጥሩ ተሳትፎ ካለው ጤናማ ህይወትን ለመምራት አያዳግተውም። በአካባቢው ላይ ለሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች ጥሩ አመለካከትና መልካም እይታ እንዲያዳብር ያግዘዋል፡፡ ጤናማ የሆነ የህይወት መርህ እንዲኖረው ከማድረግ በዘለለ ደስተኛነት የታከለበት የእለት ተእለት እንቅስቃሴ እንዲያደርግ ያግዘዋል” ሲሉ ገልፀዋል፡፡

“ህብረተሰቡን የሚጠቅም ስራ መስራት ከተወሰኑ አካላት ብቻ መጠበቅ የለበትም” የሚሉት ማስረሻ (ዶ/ር)፤ በተለይም ማህበረሰባዊ ኃላፊነት ለመንግስት አልያም ለባለሀብቶች ብቻ የሚተው ተግባር አይደለም፡፡ “ገንዘብ ስለሌለኝ ይህ የእኔ ኃላፊነት አይደለም” ብሎ መተው ሳይሆን “እጄ ላይ ያለው ምን አይነት አቅም ነው” ብሎ ማጤን እንደሚያስፈልግም ገልፀዋል፡፡

ማህበረሰቡን የሚጠቅም ተግባር ለመከወን ትውልድ ላይ መስራት እንደሚገባ የሚናገሩት ማስረሻ (ዶ/ር)፣ ልጆች የቤተሰባቸውን ፈለግ ተከትለው ያድጋሉ፡፡ መልካም ስራ እየሰራ ሰዎችን እየረዳ ህይወቱን የሚኖር ወላጅ ልጆቹም ሲያድጉ ያንኑ ፈለግ ተከታዮች ይሆናሉ። ለምሳሌ ያክል አንድ ወላጅ ልጁን ለማዝናናት ሲወጣ መንገዱ ላይ የተቸገረ ሰው ሲያገኝ አቅሙ በፈቀደ መርዳትን ማበረታታት ይገባዋል፡፡ መስጠትን ባህሉ ያደረገ ልጅ ሲያድግ ሊያዳብር የሚችለውም ይህንኑ መልካምነት  እንደሆነ አብራርተዋል፡፡

ወጣቶች የማህበራዊ ሚድያ አጠቃቀማቸውን በመቀነስና ጠቃሚ በሆኑ ጉዳዮች ላይ  ጥሩ ተሳትፎ በማድረግ ሀገራችን አሁን ላይ የጀመረችውን የልማት ጉዞ እውን የማድረግ ኃላፊነት እንደሚጠበቅባቸውም ሃሳባቸውን አጋርተዋል፡፡

በሄለን ጥላሁን

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review