“ዜጋ በጎ ሲሆን ሀገር በጎ ትሆናለች” የሚለው አባባል ስለበጎነት ከተነገሩ ወርቃማ አባባሎች መካከል ተጠቃሽ ነው። ክፍያ፣ ቀብድና ወለድ የማይጠየቅበት በጎነት በእርግጥም ከግለሰብና ከቤተሰብ ተሻግሮ ሀገርን የማቅናት ጉልበት ያለው ተግባር መሆኑ እሙን ነው፡፡
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በርካቶች በበጎ ፍቃድ አድራጎት ተግባር ላይ እየተሳተፉ ይገኛሉ፡፡ ከእነዚህ ባለቅን ልቦች መካከል ወጣት ሀያት መሐመድ አንዷ ነች። ወጠቷ በበጎ ፍቃድ አገልግሎት ላይ የተሰማራችው ድንገት ከደረሰባት ጉዳት በኋላ ሲሆን፣ “በእኔ የደረሰ በሌሎች እንዳይደርስ በማሰብ ነው የበጎ ፍቃድ አድራጎትን የተቀላቀልኩት” ትላለች፡፡
ወጣት ሀያት ተወልዳ ያደገችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ አራዳ ጊዮርጊስ ተብሎ በሚጠራ አካባቢ ነው፤ ባደገችበት አካባቢ በትምህርቷ ጎበዝ፣ በታታሪነቷና ሰዎችን በመርዳት ትታወቃለች፡፡ ታድያ ገና በወጣትነት እድሜዋ ያላሰበችው መጥፎ አጋጣሚ በህይወቷ ይደርስባታል፤ ከእለታት በአንዱ ቀን የተለመደ የእለት ተግባሯን ለመከወን በወጣችበት መንገድ ስቶ በመጣ ተሽከርካሪ ጉዳት ደረሰባት፡፡ ድንገት በደረሰባት በዚህ የመኪና አደጋም ለአካል ጉዳት ትዳረጋለች፡፡
ወጣቷ በእግሯ ላይ የደረሰውን ጉዳት በህክምና ስትረዳ ቆይታ ከህመሟ ስታገግምና ወደ መደበኛ እንቅስቃሴዋ ስትመለስ በቅድሚያ ያደረገችው የበጎ ፍቃደኝነት ስራ ላይ መሰማራት ነበር። በእሷ የደረሰው አደጋ በሌሎች እንዳይደርስ የበኩሏን አስተዋፅኦ ለማድረግ ለራሷ ቃል መግባቷን የምታስታውሰው ወጣቷ፣ ክረምት ከበጋ በተለያዩ የበጎ ፍቃድ ስራዎች እየተሳተፈች ስለመሆኗ ታስረዳለች፡፡
ከ2007 ዓ.ም ጀምሮ በበጎ ፍቃድ አገልግሎት ተሳትፎ እያደረገች እንደምትገኝ የምትገልጸው ወጣቷ፣ በመንገድ ትራፊክ ማስተባበር፣ የአቅመ ደካሞችን ቤት በማደስ፣ በደም ልገሳና መሰል የበጎ ፍቃድ አገልግሎቶች ላይ ትሳተፋለች፤ የአካባቢዋ ማህበረሰብም ተሳትፎ እንዲያደርጉ ታስተባብራለች፡፡
ወጣት ሀያት ከአዲስ ልሳን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል ጋር በነበራት ቆይታ “የአንድን ሰው ህይወት መታደግ መቻል አንድ ቤተሰብ እንደማትረፍ ይቆጠራል” ብላለች፡፡ አቅመ ደካማ ሰዎችን መንገድ በማሻገር ውስጥ የሚገኘው የህሊና እርካታ በቃላት የሚገለፅ አይደለም፤ ሌሎች ወጣቶችም ወደዚህ የበጎ ተግባር በመግባት ተሳትፎ ቢያደርጉ መልካም ነው ስትል አክላለች፡፡
የሶስት ልጆች እናት የሆኑት ሌላኛዋ በጎ ፈቃደኛ ወይዘሮ ብዙአየሁ ገረሱ እናትነት እና የቤት ውስጥ የስራ ጫና ሳይበግራቸው የአካባቢያቸውን ህብረተሰብ ሲያገለግሉ ይውላሉ፡፡ ልጅ የማሳደግ ድርብ የእናትነት ኃላፊነት ጫናን በመቋቋም በ5 ኪሎ ቅድስተ ማሪያም ቤተ ክርስቲያን አካባቢ የመንገድ ትራፊክ የማስተባበር ሰራዎችን እየሰሩ ያገኘናቸው ወይዘሮ ብዙአየሁ የቤት ውስጥ ስራቸውን ከመከወን ጎን ለጎን ባላቸው ትርፍ ጊዜ ህብረተሰቡን ለማገልገል በማሰብ በበጎ ተግባር ላይ ተሳትፎ ያደርጋሉ፡፡
“በጎነት አንዴ በውስጥ ሰርጾ ከገባ ልትተው አትችልም” የሚሉት ወይዘሮ ብዙአየሁ፣ ሁሉም ወጣቶች በበጎ ፈቃድ ስራ ላይ ተሳትፎ በማድረግ የሰዎችን ህይወት መታደግ ይገባቸዋል ባይ ናቸው።
የትራፊክ አደጋ የበርካቶችን ህይወት እየቀጠፈ፣ ለአካል ጉዳት እየዳረገ እንዲሁም ለከፍተኛ ንብረት ውድመት ምክንያት እየሆነ መጥቷል፡፡ ከመንገድ ትራፊክ አደጋ ተጎጂዎች መካከል 80 በመቶ የሚሆኑት እግረኞች እንደሆኑ የመንገድ ደህንነት የትራፊክ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ የትራፊክ ምልክቶችን አለማክበር፣ ደርቦ ማለፍ፣ ቅድሚያ አለመስጠት፣ የፍጥነት ወሰንን አለማክበር ዋነኛ የትራፊክ አደጋ መንስኤዎች ናቸው።
ክረምት ከዝናብ፣ ጭጋግ እና ጎርፍ ጋር ተያይዞ የትራፊክ አደጋ የሚበዛበት ወቅትመሆኑ ይታወቃል፡፡ ይህን የትራፊክ አደጋ ለመከላከልም በርካታ በጎ ፍቃደኛ ወጣቶች በከተማዋ የመንገድ ደህንነት ትራፊክ ቁጥጥር የበጎ ፍቃድ ስራን እያስተናበሩ እንደነበሩ ይታወቃል፡፡
በአራዳ ክፍለ ከተማ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ማስተባበሪያ ቡድን መሪ ወይዘሮ ህያብ ህሉፍ በክፍለ ከተማው በቤት ግንባታ፣ በማዕድ ማጋራት፣ በልዩ ፍላጎት ድጋፍ፣ በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር፣ በአካባቢ ጽዳት፣ ማስዋብና እንክብካቤ፣ በጎርፍ አደጋ ስጋት መከላከል፣ በከተማ ግብርና፣ በህዝብ መዝናኛ ቦታዎች ማስተባበር፣ በጎነት በሆስፒታልና በጤና ጣቢያ መርሃ ግብር፣ የደም ልገሳ፣ የመንገድ ትራፊክ አገልግሎት ፕሮግራም እና በመሳሰሉት የበጎ ፍቃድ መርሃ ግብሮች ከ94 ሺህ በላይ በጎ ፍቃደኞች ተሳትፎ ማድረጋቸውን ገልጸዋል፡፡
በክፍለ ከተማው 546 ሚሊዮን 318 ሺህ 448 ብር ግምት ያለው ሃብት በማሰባሰብ ከ62 ሺህ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ወይዘሮ ህያብ ጠቁመዋል፡፡ በመንገድ ትራፊክ ደህንነት አገልግሎት ላይ ብቻ 600 በጎ ፈቃደኞች ተሳትፎ ማድረጋቸውንም አክለው ተናግረዋል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የህብረተሰብ ተሳትፎና በጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ኮሚሽን ኮሚሽነር ወይዘሮ አስራት ንጉሴ በከተማዋ በ2017 የክረምት የበጎ ፍቃድ አገልግሎት በመንገድ የትራፊክ ማስተናበር መርሃ ግብር 8 ሺህ 475 በጎ ፍቃደኞች መሳተፋቸውን አውስተው፣ እነዚህ በጎ ፍቃደኞች በሁሉም ክፍለ ከተማ በሚገኙ መንገዶች፣ አደባባዮች እና ጎዳናዎች ላይ የትራፊክ እንቅስቃሴ እንዲሳለጥ ያስተናብራሉ፡፡
እንደ ወይዘሮ አስራት ገለጻ የበጎ ፍቃድ ፕሮግራም 18 መርሃ ግብሮች ያሉት ሲሆን፣ ከእነዚህም መካከል የቤት ግንባታ፣ ማእድ ማጋራት፣ የትምህርት ማጠናከሪያ፣ የነፃ የህክምና አገልግሎት፣ የደም ልገሳ፣ በጎነት በሆስፒታል፣ የመንገድ ትራፊክ አገልግሎት፣ የህፃናት ድጋፍ፣ የልዩ ፍላጐት ድጋፍ፣ አረንጋዴ አሻራ ተሳትፎ፣ የአካባቢ ፅዳትና ማስዋብ፣ የጐርፍ ስጋትና መከላከል መርሃ ግብሮችና ሌሎች በርካታ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ስራዎች ማህበረሰቡን በማሳተፍ መሰራታቸውን ተናግረዋል፡፡
በእነዚህ መርሃ ግብሮች ከ 2 ነጥብ 4 ሚሊዮን በላይ በጎ ፈቃደኞች በድግግሞሽ ተሳትፎ ያደረጉ ሲሆን፣ በዚህም ከ 1 ሚሊዮን 25 ሺህ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ ሆነዋል። ከተለያዩ የበጎ ፍቃድ መርሃ ግብሮችም ከበጎ ፍቃደኞች እና ባለሃብቶች 8 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር የሚገመት ሃብት መሰብሰቡን ወይዘሮ አስራት ገልጸዋል፡፡
በይግለጡ ጓዴ