በእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ተጠባቂው የሊቨርፑል እና የማንችስተር ዩናይትድ ተጠባቂ ጨዋታ ዛሬ ይደረጋል።
ሊቨርፑል ከሦስት ተከታታይ ሽንፈት ወደ ድል ለመመለስ ማንችስተር ዩናይትድ ከዘጠኝ ዓመት በኋላ በአንፊልድ ለማሸነፍ ወደ ሜዳ ይገባሉ።
በከፍተኛ የዝውውር ገንዘብ ጥራት ያላቸውን ተጫዋቾች ያመጣው ሊቨርፑል ያልተጠበቀ የአቋም መውረድ ገጥሞታል።
በርካታ ሚሊየን ፓውንድ ፈሰስ የተደረገባቸው ተጫዋቾች ብቃት አመርቂ መሆን አልቻለም።
ሊቨርፑል የምንግዜም ተቀናቃኙ ማንችስተር ዩናይትድን የሚገጥመው ከሦስት ተከታታይ ሽንፈት በኋላ ነው።
ማንም ሳይጠብቃቸው ሊቨርፑልን በመጀመሪያ የውድድር ዓመት የሊጉ ባለድል ያደረጉት አርነ ስሎት ሁለተኛ ዓመታቸውን በጥሩ መንገድ አልጀመሩም።
ኔዘርላንዳዊው ሰው በአሰልጣኝነት ታሪካቸው ለመጀመሪያ ጊዜ ሦስት ተከታታይ ሽንፈት ገጥሟችዋል።
ሊቨርፑል ምንም እንኳን ሰሞነኛ ብቃቱ ጥሩ አይሆን እንጂ በአንፊልድ አሁንም አስፈሪ ነው።
ቀዮቹ በሜዳቸው በሁሉም ውድድር ያከናወኗቸውን አምስቱንም ጨዋታዎች አሸንፈዋል።
በክሪስታል ፓላስ ፣ ጋላታሳራይ እና ቼልሲ በተከታታይ የተረቱት ከሜዳቸው ውጪ ነው።
ከሊጉ መሪ አርሰናል በአራት ነጥብ የራቀው ሊቨርፑል በዛሬው ወሳኝ ጨዋታ ግብ ጠባቂው አሊሰን ቤከርን በጉዳት ያጣል።
በመጠነኛ ጉዳት ከፈረንሳይ ብሔራዊ ቡድን ውጪ የተደረገው ተከላካዩ ኢብራሂማ ኮናቴ ለጨዋታው ዝግጁ ነው ተብሏል።
ወጥ ብቃት ማሳየት የተሳነው ማንችስተር ዩናይትድ በአንፊልድ ጥሩ ክብረወሰን የለውም።
ዩናይትድ ለመጨረሻ ጊዜ ሊቨርፑልን ከሜዳው ውጪ ያሸነፈው ከዘጠኝ ዓመት በፊት ነበር።
በሊጉ ሁለት ተከታታይ ጨዋታ ማሸነፍ ያልቻለው የዩናይትድ አሰልጣኝ ሩበን አሞሪም ከሜዳው ውጪ ካደረጋቸው ስምንት የመጨረሻ የሊግ ጨዋታዎች አንድም ማሸነፍ አልቻለም። በሁለቱ አቻ ተለያይቶ በስድስቱ ተሸንፏል።
የክለቡ ከፊል ባለድርሻ ሰር ጂም ራትክሊፍ ለሩበን አሞሪም ጊዜ ለመስጠት ዝግጁ ቢሆኑም ፖርቹጋላዊው አሰልጣኝ ጨዋታዎችን ማሸነፍ ይጠበቅበታል።
ዩናይትድ በቅርብ ዓመታት ከሊቨርፑል ጋር ያለው ክብረወሰን ግን ጥሩ አይደለም።
በመጨረሻ ካደረጋቸው 14 የፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎች ቀያይ ሰይጣናቱ ሙሉ ሦስት ነጥብ የወሰዱት በአንዱ ብቻ ነው።
ሰባቱ ጨዋታ የተጠናቀቀው በሊቨርፑል አሸናፊነት እንደሆነ የኦፕታ ቁጥራዊ መረጃዎች ያሳያሉ።
የ40 ዓመቱ ዋና ዳኛ ማይክል ኦሊቨር የሚመሩት የዛሬ ተጠባቂ ጨዋታ ምሽት 12:30 ላይ ይጀምራል።
ከዚህ ጨዋታ ቀደም ብሎ 10 ሰዓት ላይ ቶተንሃም ሆትስፐርስ አስቶንቪላን ያስተናግዳል።
በሸዋንግዛው ግርማ