የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ ከአጀንዳ ተቀባይነት ወደ አጀንዳ ሰጭነት በመሸጋገር ብሔራዊ ጥቅምን በሚያስጠብቅ ከፍታ እየተጓዘ ነው

You are currently viewing የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ ከአጀንዳ ተቀባይነት ወደ አጀንዳ ሰጭነት በመሸጋገር ብሔራዊ ጥቅምን በሚያስጠብቅ ከፍታ እየተጓዘ ነው
  • Post category:ፖለቲካ

AMN ጥቅምት 9/2018

የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ ከአጀንዳ ተቀባይነት ወደ አጀንዳ ሰጭነት በመሸጋገር ብሔራዊ ጥቅምን በሚያስጠብቅ ከፍታ እየተጓዘ እንደሚገኝ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የብሪክስ ሴክሬታሪያት ዳይሬክተርና የቀድሞው በኤርትራ የኢትዮጵያ ዲፕሎማት ዘርይሁን መገርሳ ገለጹ።

በውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት፣ የኢፌዴሪ መከላከያ ዋር ኮሌጅና በሠመራ ዩኒቨርሲቲ ትብብር የሁለቱ የውሃ ሥርዓቶችና የኢትዮጵያ ስትራቴጂካዊ ነፃነት፥ የዓባይና የቀይ ባሕር ትስስር እና የአፋር ክልልን ስትራቴጂካዊ ሚና መዳሰስ” በሚል መሪ ሃሳብ በሠመራ ዩኒቨርሲቲ ምክክር ተካሂዷል።

የኢትዮጵያ የዓባይ ቀይ ባሕር የስትራቴጂ መሠረት የጂኦ-ስትራቴጂክ ደረጃ ትንተና ጉዳዮችን የሚያትት የመነሻ ጽሁፍ ቀርቦ ምክክር ተደርጎበታል።

በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የብሪክስ ሴክሬታሪያት ዳይሬክተርና የቀድሞው በኤርትራ የኢትዮጵያ ዲፕሎማት ዘርይሁን መገርሳ፥ ታላቁ የህዳሴ ግድብና የቀይ ባሕር ጉዳይ ከፊት የተሰለፉ የብሔራዊ ጥቅም አጀንዳዎች መሆናቸውን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ ከአጀንዳ ተቀባይነት ወደ አጀንዳ ሰጭነት በመሸጋገር ብሔራዊ ጥቅምን በሚያስጠብቅ ከፍታ እየተጓዘ ነው ብለዋል።

በዚህም ኢትዮጵያ ህዳሴን በማጠናቀቅ ስጋትን በድል ቋጭታለች ያሉት ዲፕሎማቱ፥ የኢትዮጵያን ታሪካዊ፣ ተፈጥሯዊ፣ ጂኦግራፊያዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ዓለም አቀፍ ማድረግ መቻሉን ተናግረዋል።

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ፈቲህ ማህዲ(ዶ/ር፥ ዓለም አቀፍ የውሃ ሃብቶች ለአንድ ሀገር ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ወሳኝ ናቸው ብለዋል።

የኢትዮጵያን ፍትሕዊ የባሕር በር ጥያቄ በዓለም አቀፍና አሕጉር አቀፍ የዲፕሎማሲ መድረኮች ላይ ማስመዝገብ ተችሏል ሲሉም ገልጸዋል።

የባሕር መዳረሻ ሳይኖራት ኢትዮጵያ የህዝቦቿን ዘላቂ ልማትና ሁለንተናዊ ብልጽግና ማረጋገጥ አዳጋች መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ የቀይ ባሕርን የባለቤትነት ጥያቄም ሁለንተናዊ ሉዓላዊነትን በማረጋገጥ ዘላቂ የልማት ግቦችን ለማሳካት ማሰሪያ ገመድ እንደሆነ ማስረዳታቸዉን ተዘግቧል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review