በጐነት ልዩ መገለጫዋ የሆነችው አዲስ አበባ ብዙዎችን ከወደቁበት ስርቻ አንስታ የቤት ባለቤት ማድረግ ከጀመረች ዋል አደር ብላለች፡፡
በአዲስ አበባ ባህል እየሆነ በመጣው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት መስጠት እንደማያጐድል በተረዱ ቅን ልብ ባላቸው ዜጎች የብዙ አቅመ ዳካማ ዜጎች እንባ እየታበሰም ይገኛል፡፡
ወ/ሮ እቴቱ አበበ እና ወ/ሮ አልማዝ ቁምቢ ከሞቀ ቤታቸው ወጥተው ጎዳናን ቤቴ እስከማለት፣ ከራስ ስራ ወጥቶ በሰው ቤት ተቀጥሮ እስከመስራት ከዚህ እልፍ ሲልም በስተርጅና ባህር አቆርጦ እስከመሰደድ ህይወትን በብርቱ ተጋፍጠዋት ነበር፡፡ ነገር ግን ይህ ሁሉ ልፋትና ጥረት በኘላስቲክ ከተወጠረች ደሳሳ ጎጆ ሊያወጣቸው አልቻለም፡፡
ወ/ሮ አቴቴ አረብ ሃገር ለ5 አመታት ያህል በሰው ቤት ተቀጥረው ሰርተው ምንም ገንዘብ ሳይዙ ወደ ሀገራቸው ከብዙ የስቃይ ኑሮ በኃላ ባዶ እጃቸውን መመለሳቸውን ይናገራሉ፡፡

ወደ ሀገራቸው ከመጡ በኃላም ቢሆን ዝናብንና ጸሐይን በምታፈራርቀው ከኘላስቲክ በተሰራች መጠለያ ጎጆ ኑሮቸውን አደረጉ፡፡ ይህች የኘላስቲክ ጎጆ በዝናብ እና በነፋስ ብዛት በየጊዜው በላያቸው ላይ እየፈረሰች ብዙ ጊዜ ተስፋን አስቆርጣቸው ታውቃለች፡፡በተለይ ልጆቻቸው እንደሰው ተኝተው ለማደር የተቸገሩበትን ያን አስከፊ ጊዜ ሲያስታውሱ በእንባ ታጅበው ነው፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በላፍቶ ክፍለ ከተማ በተለምዶ 58 ማዞሪያ በተባለ መንደር የመኖሪያ ቤት ገንብቶ ለአቅመ ደካሞች አበርክቷል፡፡ እነ ወ/ሮ እቴቱም የዚህ እድል ተጠቃሚ ከሆኑት አቅመ ዳካሞች መካከል ይገኙበታል፡፡
አሁን ላይ ይሄ ቤት ታሪኬን ለውጦታል ይላሉ ወ/ሮ እቴቱ፤ እውነት አይመስለኝም ይህንን ቤት ለሰራልኝ ህዝብና መንግስት ለማመስገን ቃላት የለኝም፤ እንዲሁ ብቻ እድሜን ከጤና እንዲሰጣቸው እመኛለሁ ሲሉ በእንባ ታጅበው ገልፀዋል፡፡
ወ/ሮ አልማዝ እንደ ወ/ሮ እቴቱ ሁሉ ለሁለት አመታት ያህል ጥቅም ላይ ውሎ ከተጣለ ባነር የተሸፈነች የኘላስቲክ ቤታቸውን ከልለው ከዚያም አልፎ ለሚገባው የዝናብ ውሃ በሚተኙበት ወቅት ላስቲክ ለብሰውና ጃንጥላ ከልለው ይተኙ እንደነበር ይገልፃሉ ፡፡ የከፋው ደግሞ ውሃ፣መብራት፣ መፀዳጃ ባለመኖሩ ኑሮአቸው የስቃይ እንደነበረ ነው ለኤ.ኤም.ኤን ሚዲያ የተናገሩት፡፡

ከዚያ ለሰው ለጅ መኖሪያ ከማይሆን ስፍራ መውጣታች ትልቅ ደስታን ፈጥሮልናል፡፡ እስካሁን ከነበረው ጫና የተነሳ አእምሮአችን ልክ አልነበረም ነው ያሉት፤ አሁን ገና እንደ ሰው መኖር ጀመርን ሲሉ በታቅ ደስታ ገልፀዋል፡፡ ለወ/ሮ እቴቱና ወ/ሮ አልማዝ የፈነጠቀችው የአዲስ አበባ ፀሐይ ኑሮ ካሉት መቃብር ይሞቃል ለሚሉት ሁሉ የተስፋ ብርሃን ይዛ መጥታለች፡፡
የዚህ ዕድል ተጠቃሚ ከሆኑት መካከል ሙሉቀን አየነው አንዱ ሲሆን በሹፍርና ሙያው አዲስ አበባን ያለስዓት ገደብ ያካልል ነበር አልፎም ህይወትን የተሻለ ለማድርግ እና የትዳር አጋሩን የነፃነት ዘካሪያስን የታዋቂ ዘፋኝነትን ህልምን ዕውን ለማድረግ ከሹፍርናው ባሻገር ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ በጫኝና አውራጅነት ይሰራ እንደነበር ይናገራል፡፡
ነገር ግን ያ ሁሉ ሰርቶ የመለወጥ ተስፋና ጉጉት ህልም በአንዲት አጋጣሚ ተገታ፤ የቤቱ ምሶሶ ያ ለፍቶ አዳሪ በሚያሽከረክረው ተሽከርካሪ ላይ ባጋጠመው የቴክኒክ ብልሽት በደረሰበት አደጋ ከአልጋ ላይ ለመዋል ተገደደ፡፡
በሚኖርበት ደሳሳ ጎጆ ከአመት አመት የመፀዳጃ ቤት ፍሳሽ እየፈሰሰ ከህመሜ ባሻገር በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ሆነብኝ ነበር ይላል፡፡ ኑሮዬ አደጋው ከደረሰብኝ ከ2ዐ14 ዓ/ም ወዲህ ሲኦል ሆኖብኛል ቆይቷል የሚለው ሙሉቀን፡፡ አሁን ግን የከተማ አስተዳደሩ በአመቻቸው የቤት ባለቤት ዕድል ተጠቃሚ መሆን በመቻሌ ችግሬን ሁሉ ቀርፎልኛል፤ ዛሬ ያማረና ምቹ መኖሪያና መፀዳጃ ቤት አለኝ እንደሰው መኖርም ሆነ መፀዳዳት ችያለሁ ለእኔ ይሄ እንደገና እንደመፈጠር ነው ሲል ለኤ ኤም ኤን ተናግሯል፡፡
በበረከት ጌታቸዉ