ኢትዮጵያ እና ኳታር የኢንቨስትመንት እና የልማት ትብብራቸውን ለማጠናከር ተስማምተዋል።
የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ ከዓለም ባንክ እና ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይ ኤም ኤፍ) ዓመታዊ ስብሰባ ጎን ለጎን ከኳታር አቻቸው አሊ ቢን አህመድ አል ኩዋሪ እና ከኳታር የልማት ፈንድ ዋና ዳይሬክተር ፋሃድ ሃማድ አል ሱለይቲ ጋር ተወያይተዋል።
በውይይታቸውም በሁለቱ ሀገራት መካከል በመሠረተ ልማት፣ በኢንቨስትመንትና በልማት ስራዎች የጋራ ተጠቃሚነታቸውን የሚያረጋግጥ ስትራቴጂያዊ አጋርነትን ለመፍጠርና ያላቸውን ትብብር ማሳደግ በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ መክረዋል፡፡
የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሽዴ በውይይቱ ወቅት ኢትዮጵያ ከኳታር ጋር አጋርነቷን ለማጠናከር ያላትን ቁርጠኝነት ገልፀው፤ በኢትዮጵያ ያሉትን የኢንቨስትመንት እድሎች አስረድተዋል፡፡
የኳታር ባለሀብቶች በኢትዮጵያ በተለይም በአምራች ኢንዱስትሪ፣ በግብርና፣ በቱሪዝም እና ሌሎች ዘርፎች እንዲሰማሩ የዪትጵያ መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚደረግም ገለጸዋል፡፡
የኳታር የገንዘብ ሚኒስትር አሊ ቢን አህመድ አል ኩዋሪ በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ማሻሻያ ተግባራት አድንቀው በንግድና የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ላይ በትብብር ለመስራት ኳታር ያላትን ፍላጎት ገልፀዋል፡፡
የኳታር የልማት ፈንድ ዋና ዳይሬክተር ፋሃድ ሃማድ አል ሱለይቲ በውይይቱ ወቅት፤ የኳታር የልማት ፈንድ አካታች እድገትን ለማረጋገጥ እንዲሁም ንግድና ኢንቨስትመንትን ለማሳደግ የሚያስችሉ ፕሮጀክቶችን ለመደገፍ ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡
ሃገራቱ በመካከላቸው ጥልቅና የረጅም ጊዜ ትብብር ለመፍጠርና ጠንካራ የልማት ፕሮጀክቶችን ለመለየት እንዲቻል የጋራ የቴክኒክ ቡድን ለማቋቋም ቁርጠኛ መሆናቸውን አረጋግጠዋል፡፡