የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የ2018 በጀት አመት 1ኛ ሩብ አመት እቅድ አፈጻጸም ግምገማ አካሂዷል።
ከተማ አስተዳደሩ ባካሄደው ግምገማ መድረክ ላይ በመዲናዋ ባለፉት 3 ወራት 138 ፕሮጀክቶች ተጠናቀው ለህብረተሰቡ አገልግሎት ክፍት መደረጋቸውን የአዲስ አበባ ከተማ ዲዛይንና ግንባታ ስራዎች ቢሮ አማካሪ አቶ አህመድ ሂሶን ተናግረዋል።
በከተማ አስተዳደሩ የሩብ አመቱ የ90 ቀናት እቅድ ክንውን ግምገማ በመንገድ እና በመሰረተ ልማት ዝርጋታና አቅርቦት የተከናወኑ ተግባራት የተሻለ ዉጤት የተገኘባቸው እንደነበሩ ተነስቷል።
በሩብ አመቱ ከተከናወኑት የልማት ስራዎች መካከል፣ ያለጥገና ረጅም አመታትን ያስቆጠረው የለገዳዲ ወንዝ ግድብ የውሃ ማሰራጫ፣ ከውጪ እቃዎችን በመግዛት ጭምር ሰፋፊ የጥገና ሥራዎች ከተደረጉላቸው ፕሮጀክቶት መካከል እንደሚገኝበት ተመላክቷል።
የጥገናና የማስፋፊያ ስራውም ወደ መጠናቀቁ ደረጃ ላይ መድረሱን እና ባሳለፍነው ክረምት በተሰራው የማስፋፊያ እና የጥገና ስራ በቀን እስከ 15 ሺህ ሜትር ኩብ ተጨማሪ ውሃ ማግኘት እንደሚቻል የአዲስ አበባ ከተማ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን ዋና ስራ አስፈጻሚ ኢንጂነር ዘሪሁን አባተ ጠቁመዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ሙህዲን ረሻድ (ኢ/ር) በበኩላቸው፣ በሩብ አመቱ 300 ኪሎ ሜትር የመንገድ ዝርጋታ ለመስራት እቅድ ተይዞ እንደነበር አንስተው፣ በመንገድ ዝርጋታ፣ በጥገና፣ በኮብል ንጣፍ፣ ወደ 368 ኪሎ ሜትር በመስራቱ ከእቅድ በላይ ውጤት መመዝገቡን ተናግረዋል።
አስተዳደሩ ከመንገድ ልማት አቅርቦት እና ዝርጋታ ባለፈ፣ በአረንጓዴ ልማት እና በፕሮጀክት አፈጻጸምም ስኬት የተመዘገበበት እንደነበር አመላክቷል።
የአዲስ አበባ ከተማ ውበት እና አረንጓዴ ልማት ምክትል ቢሮ ኅላፊ ወይዘሮ ጸሃይ ጌታሁን በበኩላቸው፣ በአዲስ አበባ ያለምንም ወጪ እና በራስ አቅም እንዲሁም በህብረተሰብ ተሳትፎ ከ6 ሚሊዮን በላይ ችግኞችን አዘጋጅቶ በመትከል ከፍተኛ አፈጻጸም መመዝገቡን ተናግረዋል።
ወይዘሮ ጸሃይ አክለውም፣ በአዲስ አበባ በሁሉም ኮሪደሮች ማለትም በ6ቱ የኮሪደር ልማት ስራዎች እና በ2ቱ የወንዝ ዳርቻ ልማት በተሰሩት ስራዎች ከፍተኛ አፈጻጸም በመመዝገቡ፣ ለህብረተሰቡ የተሻለ የመኖሪያ ስፍራን እና ምቹ ሁኔታዎች መፍጠር መቻሉን ጠቁመዋል።
በሩብ አመቱ ማለትም በአጭር ጊዜ ውስጥ በርካታ ስራዎችን መስራት የሚቻልበት ተቋም እየተገነባ መሆኑን እና ባለፉት 3 ወራት ብቻ 138 ፕሮጀክቶች ተጠናቀው ለህብረተሰቡ ለአገልግሎት ክፍት መደረጋቸውን የአዲስ አበባ ከተማ ዲዛይንና ግንባታ ስራዎች ቢሮ አማካሪ አቶ አህመድ ሂሶን ተናግረዋል።
በቀጣይም የከተማዋ ነዋሪዎች የሚያነሷቸው የልማት እንዲሁም የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ተገቢው እና ፈጣን ምላሽ እንዲያገኙ በትኩረት እንደሚሰራ አቅጣጫ የተቀመጠ መሆኑን እና ለዚህም መሳካት አመራሩ ከህዝብ ጋር በሚያደርገው ተሳትፎ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተገልጿል።
በወርቅነህ አቢዮ