ከሩስያ ጋር በማንኛውም ቦታ እና ሁኔታ ለመደራደር ፍቃደኛ መሆናቸውን የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ተናገሩ

You are currently viewing ከሩስያ ጋር በማንኛውም ቦታ እና ሁኔታ ለመደራደር ፍቃደኛ መሆናቸውን የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ተናገሩ

AMN- ጥቅምት 10/2018 ዓ.ም

የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዘለንስኪ ተኩስ አቁምን ባማከለ መልኩ ከሩስያ ጋር ለመደራደር ፍቃደኛ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ባሳለፍነው አርብ በኋይት ሀውስ ከዶናልድ ትራምፕ ጋር የተወያዩት ዘለንስኪ፤ ከሩስያው ፕሬዝዳንት ጋር ጦርነቱን ለማቆም በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ዙሪያ ለመምከር ዝግጁነታቸውን ገልጸዋል።

በዩክሬን ውጊያ እያካሄደ የሚገኘው የሩስያ ጦር ባለበት እንዲቆም ትራምፕ ያቀረቡትን ሀሳብ እንደሚቀበሉ የተናገሩት ዘለንስኪ፤ የጦርነቱን መስፋፋት ለመግታት አስቸኳይ ተኩስ አቁም እንደሚያስፈልግ ነው የገለጹት።

ዘለንስኪ ከነጩ ቤት ቆይታ በኃላ ከጋዜጠኞች ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ “ዲፕሎማሲያዊ እና ሰላማዊ ውይይቶች ፍሬ እንዲያፈሩ ጦርነቱ ባለበት ሊቆም ይገባል ሮኬት እና ሚሳኤል እየዘነበ ስለ ሰላም ማውራት ከባድ ነው” ብለዋል።

ከፕሬዝዳንት ፑቲን ጋር በሁለትዮሽ ወይም በሶስትዮሽ መንገድ ለመደራደር ዝግጁ እንደሆኑ የገለጹት ዘለንስኪ፤ ፑቲን እና ትራምፕ በሀንጋሪ ለመገናኘት ባሰቡት ቀጠሮ ግብዣ ከቀረበላቸው ለመታደም ፍቃደኛ እንደሆኑም ተናግረዋል።

የምስራቅ አውሮፓውን ጦርነት ለማስቆም ደፋ ቀና እያሉ የሚገኙት ትራምፕ፤ ጦርነቱ እንዲቆም ዩክሬን አንዳንድ ግዛቶቿን ለመተው ዝግጁ ልትሆን እንደሚገባ በማሳሰብ ላይ ይገኛሉ።

ሞስኮ በበኩሏ በጦርነቱ ከዩክሬን ለወሰደቻቸው ግዛቶች እውቅና እንዲሰጥ ፣ ኪየቭ የሰሜን አትላንቲክ ቃልኪዳን ድርጅት ኔቶን እንደማትቀላቀል ማስተማመኛ እንድትሰጥ፣ እንዲሁም ከአውሮፓ ሀገራት የጦር መሳሪያ ከመቀበል እንድትቆጠብ ቅድመ ሁኔታ አስቀምጣለች።

በዳዊት በሪሁን

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review