በመንግስት አስተባባሪነት 50 ሺህ በላይ ቤቶችን ለመገንባት የሚያስችል ዝግጅት ማጠናቀቁን የአዲስ አበባ ከተማ ቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ ገለጸ፡፡
ቢሮው ይህን የገለጸው በአዲስ አበባ ምክር ቤት ለመሬትና ግንባታ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የ2018 በጀት አመት የአንደኛውን ሩብ አመት አፈጻጸሙን ባቀረበበት ወቅት ነው።
የ2018 በጀት አመት የአንደኛውን ሩብ አመት አፈጻጸም ያቀረቡት የቢሮው ኃላፊ ወ/ሮ ቅድስት ኃይለጊዮርጊስ፤ ቢሮው በዝግጅት ምዕራፍ የቤት ልማት አማራጮችን በማስፋት የቤት አቅርቦቱን ማሳደግ የሚያስችል ተግባራትን ማከናወኑን ጠቅሰዋል።
በዚህም በመንግስት አስተባባሪነት 50 ሺህ 305 ቤቶችን፤ በመንግስትና በግል አጋርነት ደግሞ 97 ሺህ ቤቶችን ለመገንባት የሚያስችል ዝግጅት ተጠናቋል ብለዋል ኃላፊዋ።
በማህበር የተደራጁ 65 ማህበራትም ከ5 ሺህ በላይ ቤቶች ግንባታን መጀመራቸውን ነው የገለጹት።
የመንግስት ሰራተኞችን ከቤት ልማቱ ተጠቃሚ ለማድረግ የሚያስችል የዲዛይን ጥናት መጠናቀቁም ተመላክቷል።
የመሬትና ግንባታ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዶ/ር አቶሚ አበበ በበኩላቸው፤ ቢሮው የመምህራንን የቤት ልማት ጨምሮ የዜጎችን የመኖሪያ ቤት ጥያቄ ለመመለስ የጀመረው ተግባር የሚበረታታ ነው ብለዋል።
አገልግሎትን በማዘመን እና ፕሮጀክቶችን በቴክኖሎጂ ታግዞ በመምራት ረገድም የተሻለ አፈጻጻም መታየቱን ገልፀዋል፡፡
በጋራ መኖሪያ ቤቶች የመሰረተ ልማት አቅርቦትን ማሟላትም በቀጣይ ትኩረት ተደርጎበት በቅንጅት መስራት እንደሚገባም ነው ዶ/ር አቶሜ ያሳሰቡት።
በፈቃዱ መለሰ