ሐሰተኛ ማህተሞችንና ቲተሮችን በመጠቀም ሀሰተኛ ሰነዶችን ሲያዘጋጁ የነበሩ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ አስታወቀ።
የቦሌ እና የኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያዎች በጥናት ላይ ተመስርተው ባደረጉት ክትትል የልዩ ልዩ ተቋማትን ሀሰተኛ ሰነዶችን ሲያዘጋጁ የነበሩ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር ማዋላቸውን ገልፀዋል፡፡
አላዛር ሠለሞን የተባለውን ወንጀል ፈፃሚ ተከራይቶ በሚኖርበት ቤት ውስጥ የተለያዩ የመንግስት እና የግል ተቋማትን ሀሰተኛ ማህተሞችና ቲተሮችን በመጠቀም ልዩ ልዩ ሀሠተኛ ሰነዶችን እንደሚያዘጋጅ ፖሊስ የደረሰውን መረጃ መነሻ በማድረግ እና አስፈላጊውን መረጃ ያሰባስባል፡፡
የህግ አግባብነትን ተከትሎ ባደረገው ብርበራም ብዛታቸው 50 የሚሆኑ የተለያዩ ተቋማት ማህተሞችና ቲተሮች እንዲሁም ሀሰተኛ ሰነዶችን ለማዘጋጀት ሲጠቀምበት የነበረ ኮምፒውተር፣ ፕሪንተር እና ሌሎች ቁሳቁሶችን ጭምር በኤግዚቢትነት ይዞ ምርመራው መቀጠሉን የቦሌ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ አስታውቋል፡፡
ከተያዙት ሀሰተኛ ሰነዶች መካከል የኤሚግሬሽንና የዜግነት ጉዳዮች መስሪያ ቤት፣ የአዋሽ እና የንብ ኢንተርናሽናል ባንኮች ልዩ ልዩ ሰነዶች ጨምሮ የክልልና የዞን አስተዳደር ሰነዶች እንደተያዘ ታውቋል፡፡
በተመሳሳይ ዜና የኮልፌ ቀራናዮ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ባደረገው ክትትል በክፍለ ከተማው ወረዳ 4 ልዩ ቦታው ዓለም ባንክ አካባቢ ዘሪሁን ገ/ማርያም፣ ምንተስኖት ለማ፣ ፀጋዬ ጋዲሳ እና በአንተ አምላክ ግርማ በመኖሪያ ቤት ውስጥ የተለያዩ ሀሰተኛ ሰነዶችን ሲያዘጋጁ እጅ ከፍንጅ ይዞ ምርመራ እያጣራ መሆኑን መምሪያው ገልጿል፡፡
የኮልፌ ቀራንዮ ክ/ከተማ የአስራ አንዱም ወረዳዎች፣ የአዲስ ከተማ ክ/ከተማ የወረዳ 13፣ የጉለሌ ክ/ከተማ የወረዳ 5፣ የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክ/ከተማ የወረዳ 1 እና 2 የነዋሪነት መታወቂያዎች፣ የሸገር ከተማ አስተዳደር የፉሪ ክ/ከተማ የወረዳ 2፣ የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት፣ የስልጤ ዞን ክብ ማህተሞች፣ የልደት ካርዶች፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የትምህርት ማስረጃዎች፣ የሰነዶች ማረጋገጫ ልዩ ልዩ ሰነዶች እንዲሁም ሀሰተኛ ሰነድ ለማዘጋጀት የሚጠቀሙባቸው ሁለት ፕሪንተሮች፣ ሁለት ኮምፒተሮች፣ አንድ ላፕቶፕ፣ ሦስት የመታወቂያ መቁረጫ መሳሪያ በኤግዚቢትነት ተይዟል፡፡
ከወንጀል ድርጊቱ ጋር በተያያዘም ተሳትፎ ያላቸውን አብረሐም ጋዲሳ፣ ታጋይ ታደስ፣ መንገሻ ሺመልስ፣ ገ/ማርያም አመርጋ፣ ሚፍታ ጁሀር፣ ዩሀንስ ተስፋዬ፣ ገነት ዋለልኝ፣ ይታገሱ አያሌው፣ ፈሪዲሳ መገርሳ የተባሉ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ከአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ ያገኘነዉ መረጃ ያመላክታል፡፡