የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ የሶስተኛ ሳምንት ጨዋታዎች ትናንት ምሽት ተጀምረዋል፡፡ ዘጠኝ ጨዋታዎች በአውሮፓ የተለያዩ ከተሞች ተደርገዋል፡፡
ከእነዚህ ጨዋታዎች መካከል አንዱ ምንም ግብ አልተቆጠረበትም፡፡ ቀሪ ስምንት ጨዋታዎች በድምሩ 43 ግቦች ተቆጥረውባቸዋል፡፡ በየጨዋታው 4 ነጥብ 78 ግቦች ተመዝግበዋል፡፡
ትናንት የተቆጠሩ ግቦች ብዛት እ ኤ አ በ2014 ከተመዘገበው ቀጥሎ የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ የምንጊዜውም በርካታ ግቦች የተቆጠሩበት ምሽት ሆኗል፡፡ በዚያን ጊዜ በስምንት ጨዋታዎች 40 ግቦች ነበር የተቆጠሩት፡፡ ይህም በየጨዋታው አምስት ግቦች እንደማለት ነው፡፡
ኤርሊንግ ብራውት ሃላንድ ግብ ማስቆጠሩን ወደ 12 ተከታታይ ጨዋታዎች ያሳደገው ትናንት ምሽት ነው፡፡ በክረምቱ የዝውውር ወቅት በ64 ሚሊዮን ፓወንድ አርሰናልን የተቀላቀለው ቪክቶር ጊዮኬሬሽ ከሰባት ጨዋታዎች በኋላ ለአርሰናል ግብ ያስቆጠረውም ትናንት ምሽት ነው፡፡
በተከናወኑ ዘጠኝ ጨዋታዎች አምስት ቀይ ካርዶች ተመዘዋል፡፡ የካዛኪስታኑ ካይራት ከቆጵሮሱ ፓፎስ ጋር ባደረገው ጨዋታ ዣኦ ኮሪያ ከፓፎስ በኩል ገና በአራተኛው ደቂቃ ነበር በቀይ ካርድ ከሜዳ የወጣው፡፡
የኦሊምፒያኮሱ ሳንቲያጎ ሄዜ በቀይ ካርድ በመውጣቱ የግሪኩ ክለብ በርካታ ግቦች ተቆጥረውበት ተሸንፏል፡፡ ዘጠኝ ግቦች በተቆጠሩበት የጀርመን ጨዋታ ባየር ሊቨርኩሰን ሮበርት አንድሪችን ፒ ኤስ ጂ ኢሊያ ዛባርኒዪን በቀይ ካርድ አጥተዋል፡፡
የአንቶኒዮ ኮንቴው ናፖሊ በፊሊፕስ አሬና በፒ ኤስ ቪ ግማሽ ደርዘን ግቦች ሲቆጠሩበት ሎሬንዞ ሉካን በ76ኛው ደቂቃ በቀይ ካርድ አጥቷል፡፡ የጣሊያኑ ክለብ ሶስት ግቦች የተቆጠሩበት አጥቂው በቀይ ካርድ ከወጣ በኋላ ነው፡፡
በትናንት ምሽቱ የምድብ ጨዋታዎች ስድስት ፍጹም ቅጣት ምቶች ተሰጥተዋል፡፡ አምስቱ ወደ ግብነት ሲቀየሩ አንድ ተስቷል፡፡ ላሚን ያማል ለባርሴሎና፣ አዩብ ኢል ካቢ ለኦሊምፒያኮስ፤ ራሚ ቤንሴባይኒ ለቦርሲያ ዶርትሙንድ፣ ሃካን ቻላሃንግሉ ለኢንተር ሚላን እና አሌክስ ጋርሺያ ለባየር ሊቨርኩሰን በፍጹም ቅጣት ምት ግብ ያስቆጠሩ ተጨዋቾች ናቸው፡፡
የባየር ሊቨርኩሰኑ አሌሃንድሮ ግሪማልዶ ትናንት ምሽት ፍጹም ቅጣት ምት ያባከነ ብቸኛው ተጨዋች ነው፡፡ የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ የሶስተኛ ሳምንት ቀሪ ዘጠኝ ጨዋታዎች ዛሬ ምሽት ይደረጋሉ፡፡ ዛሬስ ምን ይከሰት ይሆን?
በታምራት አበራ