የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ የጋዛን ተኩስ አቁም አፈጻጸም በሚከታተለው ጥምር ጦር ውስጥ የቱርክን መካተት እንደሚቃወሙ ተናግረዋል።
በአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሀሳብ አቅራቢነት በጊዜያዊ ተኩስ አቁም ላይ የሚገኙት ሀማስ እና እስራኤል ወደ ሁለተኛው ምዕራፍ የተኩስ አቁም ስምምነት አፈጻጸም እንዲሸጋገሩ በአሜሪካ ግፊት እየተደረገባቸው ነው።
በቴልአቪቭ ከትላንት ጀምሮ ጉብኘት ላይ የሚገኙት የአሜሪካ ምክትል ፕሬዝዳንት ጄዲ ቫንስ ከጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታንያሁ ጋር በተኩስ አቁሙ አፈጻጸም ዙሪያ መክረዋል።
በውይይቱ ወቅት በሁለተኛው ምዕራፍ የሰላም ስምምነት ዙሪያ ቱርክ ገንቢ ሚና እንደሚኖራት ምክትል ፕሬዝዳንቱ ተናግረዋል።
ሀማስ ትጥቅ እንዲፈታ የሚጠይቀው እና ሌሎችም ቁልፍ ነጥቦችን ያካተተው የሁለተኛው ምዕራፍ የሰላም ስምምነት ሀሳብ ምን ያህል ተግባራዊ ሊሆን ይችላል የሚለው በብዙዎች ዘንድ እያነጋገረ ይገኛል።
በዚህ ስምምነት መሰረት ሁለቱ ተፋላሚዎች በዘላቂነት ጦርነቱን ለማቆም እንደሚስማሙ ቀጥሎም በአሜሪካ የሚመራ 200 ወታደሮችን ያካተተ ከተለያዩ ሀገራት የተውጣጣ ጥምር ጦር የተኩስ አቁምን አፈጻጸም ይከታተላል።
ከዚህ ባለፈም ይህ ጦር የአካባቢ ጸጥታ እና ደህንነት የሚያስከብሩ የፖሊስ አባላትን የማሰልጠን ሚና የሚኖረው ይሆናል።
ቱርክ በበኩሏ በአሜሪካ በሚመራው ጥምር ጦር ውስጥ ወታደሮቿ ሊሳተፉ እንደሚችሉ እና ከጸጥታ አገልግሎት ባለፈ በሰብአዊ ድጋፍ ላይ ሊሰማሩ እንደሚችሉ ፍንጭ ሰጥታለች።
በአንድ ወቅት ጠንካራ ዲፕሎማሲያዊ እና ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት የነበራቸው ቱርክ እና እስራኤል በአሁኑ ወቅት በዲፕሎማሲያዊ ውዝግብ ውስጥ ይገኛሉ።
የጋዛ ጦርነት መጀመርን ተከትሎ በቴልአቪቭ ላይ ጠንካራ ትችት የምትሰነስረዘው አንካራ የሁለትዮሽ የንግድ ግንኘነቷን አቋርጣለች።
በዳዊት በሪሁን