ቦሌ ክፍለ ከተማ ጃክሮስ ተብሎ በሚጠራዉ አካባቢ የዘረፋ ወንጀል ፈፅመው ለማምለጥ የሞከሩ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ

You are currently viewing ቦሌ ክፍለ ከተማ ጃክሮስ ተብሎ በሚጠራዉ አካባቢ የዘረፋ ወንጀል ፈፅመው ለማምለጥ የሞከሩ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ

AMN ጥቅምት 12 ቀን 2018 ዓ/ም

የዘረፋ ወንጀል ፈፅመው ለማምለጥ የሞከሩ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተጣራ እንደሚገኝ የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ ገለፀ፡፡

ተጠርጣሪዎቹ የፀጥታ አካል የሚመስል የደንብ ልብስ በመልበስ የዘረፋ ወንጀል ፈፅመው በቁጥጥር ስር የዋሉት ጥቅምት 11 ቀን 2018 ዓ/ም በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 14 ጃክሮስ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ነው፡፡

አብርሃም አሸናፊ እና ዳግም ብርሃን የተባሉት ሁለት ተጠርጣሪዎች ወንጀሉን የፈፀሙት ረድኤት አህመድ በተባለች ግለሰብ ላይ እንደሆነ ከቦሌ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

የግል ተበዳይ በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ወረዳ 3 ልዩ ቦታው አባ ሳሙኤል መቶ አርባ ሰፈር ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የሚገኝ የንግድ ሱቋን ዘግታ በመውጣት የሰሌዳ ቁጥር ኮድ 2B- 88595 አ.አ የሆነ ተሽከርካሪ እያሽከረከረች ስትጓዝ ከጥቂት ሜትሮች ጉዞ በኋላ እንዳስቆሟት ታውቋል፡፡

ተጠርጣሪዎቹ የግል ተበዳይን ከሾፌር መቀመጫ ላይ አስወርደው ከኋላ እንድትቀመጥ ካደረጉ በኋላ ተሽከርካሪውን ራሳቸው እያሽከረከሩ በሚፈልጉት አቅጣጫ እንደወሰዷት እና 500 ሺህ ብር ወደ አካውንታቸው እንድታስገባ እንዳስገደዷት የምርመራ መዝገቡ ያስረዳል፡፡

የግል ተበዳይ የተጠየቀችውን ያህል ገንዘብ እንደሌላት ስትገልፅላቸው በወቅቱ በእጇ ይዛው የነበረውን 8ሺህ 700 ብር ጥሬ ገንዘብ እና ሁለት ሞባይል ስልኮችን ዘርፈው እሷን ካስወረዱ በኋላ መኪናውን እየነዱ በተቃራኒ አቅጣጫ ተጉዘውለማምለጥ ሲሞክሩ ከሌላ ተሽከርካሪ ጋር ተጋጭተው የትራፊክ አደጋ አድርሰዋል፡፡

ከአደጋው በኋላ ከተሽከርካሪው ወርደው በመሮጥ ሰው ቤት ገብተው ሊሰወሩ ቢሞክሩም ሳጅን ፋንታሁን አለምነህ በተባለ የአዲስ አበባ ፖሊስ ሞተረኛ ትራፊክ እና በህብረተሰቡ ትብብር ከነ ኤግዚቢቱ በቁጥጥር ስር ውለዋል፡፡

ግለሰቦቹ ከፀጥታ አካል ጋር ተመሳሳይነት ያለው የደንብ ልብስ ይልበሱ እንጂ የፀጥታ አካል እንዳልሆኑ መረጋገጡን እና ከወንጀሉ ጋር ተያይዞ ተጨማሪ ምርመራ እየተካሄደ መሆኑን የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ ገልጿል፡፡

የፀጥታ አካል በመምሰል እና ተመሳሳይነት ያለው የደንብ ልብስ በመልበስ ወንጀል የሚፈፅሙ ግለሰቦች ሊያጋጥሙ እንደሚችሉ ህብረተሰቡ ተገንዝቦ አጠራጣሪ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙት ለሚመለከተው የፀጥታ አካል ጥቆማ እና መረጃ በመስጠት ትብብሩን እንዲያጠናክር የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ ለኤኤምኤን በላከዉ መረጃ ጥሪውን አቅርቧል፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review